አፍሪካ በዌልዲንግ ዘርፍ ያላትን ትልቅ አቅም ለመጠቀም የሀገራት የጋራ ስራ ሊጠናከር ይገባል

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 9/2017 (ኢዜአ)፡-አፍሪካ በዌልዲንግ ዘርፍ ያላትን ትልቅ አቅም ለመጠቀም የሀገራት የጋራ ስራ ሊጠናከር እንደሚገባ የፌዴራል ቴክኒክ ሙያ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

ከሚያዝያ 6 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው ሶስተኛው የአፍሪካ ዌልዲንግ ፌደሬሽን ዓመታዊ ጉባኤና ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ የማጠቃለያ መርሃ-ግብር ተካሄዷል።


 

በመርሃ-ግብሩ ላይ የአፍሪካ ዌልዲንግ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ሐመድ አቡደል አሊም፣የፌደራል ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር)ን ጨምሮ ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።

የፌዴራል ቴክኒክ ሙያ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፥ ጉባኤው ስኬታማ ነበር።

በጉባኤው ለዌልዲንግ ዘርፍ ስኬታማነት አስተዋፅኦ የሚያደርጉ ፍሬያማ ውይይቶች የተደረጉበት እንዲሁም አፍሪካ በብየዳ ሙያ ያላትን ትልቅ አቅም ያሳየችበት መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የአፍሪካ ሀገራት ትስስራቸውን በማጠናከር ዘርፉን በጋራ ለማሳደግ ቁርጠኝነታቸውን ያረጋገጡበት ነው ብለዋል።


 

የአፍሪካ ዌልዲንግ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ሐመድ አቡደል አሊም፥ ኢትዮጵያ ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት ሰጥታ ጉባኤውን በተደራጀ ሁኔታ በማዘጋጀቷ ምስጋናቸውን ገልጸዋል።

ጉባኤው በአህጉሪቱ ስላለው የዌልዲንግ አቅም ግንዛቤ የተፈጠረበት፣ ዘርፉን ለማጠናከር ትምህርት የተገኘበትና በጋራ መስራት እንደሚገባ መግባባት የተደረሰበት መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በጉባኤው አፍሪካውያን የዌልዲንግ ልምዳቸውን የተለዋወጡበትና በዘርፉ ተጨማሪ እውቀት የቀሰሙበት መሆኑን የተናገረችው በጉባኤው የተሳተፈችው ደቡብ አፍሪካዊቷ ኮንፊዲ ሎኮንዴ ናት፡፡


 

ጉባኤው የዌልዲንግ ባለሙያዎችን አቅም በማሳደግ በኩል ወሳኝ እንደነበር በማንሳት፥ ኩባንያዎች በዘርፉ መዋዕለ ንዋያቸውን ፈሰስ በማድረግ ለዘርፉ ዕድገት እንዲሰሩም ጠይቃለች።

በጉባኤው በተካሄዱ ውድድሮች ያሸነፉ ግለሰቦች እውቅና የተሰጣቸው ሲሆን፥ አራተኛውን የአፍሪካ ዌልዲንግ ፌደሬሽን ጉባኤ ደቡብ አፍሪካ እንደምታስተናግድ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም