በዲጂታል መሰረተ ልማት የአገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማሳለጥ የሚያስችል አቅም ተፈጥሯል - የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በዲጂታል መሰረተ ልማት የአገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማሳለጥ የሚያስችል አቅም ተፈጥሯል - የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 9/2017(ኢዜአ)፡- በዲጂታል መሰረተ ልማት የአገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል፣ የሥራ ዕድል እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማሳለጥ የሚያስችል አቅም መፈጠሩን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
በኢትዮጵያ በዲጂታል መሰረተ ልማት እና ስታርት አፕ ሀገራዊ ኢኮኖሚ እድገትን ማምጣት የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ በዲጂታል መሰረተ ልማት አዳዲስ እድሎችን የሚያመጡ ስታርት አፖች፣ ኢ -ኮሜርስና ዲጂታል መታወቂያ ውጤት እያስገኙ ነው፡፡
የዲጂታል መሰረተ ልማት በተስፋፋባቸው አካባቢዎች አርሶ አደሮች፣ ሸማቾች፣ የቢዝነስ ባለቤቶችን እና ሌሎችን በአንድ ላይ የሚያገናኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም የዲጂታል መሰረተ ልማተ ዝርጋታ የተሳለጠ ንግድ ሥርዓትን መገንባት፣ ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ መፍጠር እንዲሁም የአገልግሎት አሰጣጡን ማሻሻል አስችሏል ብለዋል፡፡
ለንግድና ኢንቨስትመንት የተመቸ ስነ ምህዳር በመፍጠር መንግስት ለዲጂታል መሰረተ ልማት ያወጣውን ወጪ መተካት የሚያስችል አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአምስት ሚሊዮን ኮደርስ ስልጠና የወጣቶችን እውቀትና ክህሎት ማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የተለያዩ ፈተናዎችን አልፈው ወደ 2ኛ ደረጃ ከተሸጋገሩ 92 ስታርት አፖች መካከል እስከ 700 ሚሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡
እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ2018 የስታርት አፖች ሀብት ግምት ስድስት ሚሊዮን ዶላር እንደነበር አስታውሰው፤ ካሉት ከሁለት ሺህ በላይ ስታርት አፖች የ513ቱ ብቻ ከ303 ሚሊዮን ዶላር መሻገሩን ገልጸዋል፡፡
በዲጂታል መሰረተ ልማት ከ30 ሺህ 422 በላይ የሥራ ዕድል መፈጠሩን ገልጸው፤ በዘርፉ የሚፈጠረው የሥራ ዕድል እውቀትን መሰረት ያደረገ ዓለም አቀፍ ካምፓኒዎችን መፍጠር የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በፈጠራ የታገዘ ችግር ፈቺ ኢንዱስትሪዎችን እንደምትፈልግ የገለጹት ዶክተር ባይሳ ፤ ለዚህ ደግሞ ኢንዱስትሪዎች በምርምርና ልማት መደገፍ አለባቸው ብለዋል፡፡
በዚህም የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪውን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሚያደርጉ የምርምር ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢንዱስትሪዎችን በራሳችን የሰው ሀይል መተካት የሚያስችል የቴክኖሎጂ ሽግግር እየተፈጠረ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ከውጭ የሚገቡ የኢንዱስትሪ እቃዎች በሀገር ውስጥ ምርት እየተተኩ መሆኑን አክለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለወረቀት በዓመት እስከ 44 ቢሊዮን ብር ታወጣ እንደነበር አስታውሰው፤ ከውጭ የሚገባውን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የሚያስችል የቴክኖሎጂ ምርምር ሥራ ተከናውኖ ውጤት አስገኝቷል ብለዋል፡፡