ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ ትቀጥላለች -ኢንጂነር አይሻ መሀመድ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ ትቀጥላለች -ኢንጂነር አይሻ መሀመድ

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 9/2017 (ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ጋር ያላትን የቆየ ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ ገለጹ።
የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ፥ ከተሰናባቹ የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ /ICRC/ ልዑካን ቡድን መሪ ብሩስ ሎሪየንዝን ዛሬ በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
ውይይቱ ኢትዮጵያ እና የቀይ መስቀል ኮሚቴው ባላቸው ትብብር እና የሰብዓዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው።
በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለውን የቆየ አጋርነት ይበልጥ ለማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይም መክረዋል፡፡
የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ፥ የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ በኢትዮጵያ እያደረገ ላለው ድጋፍ ያላቸውን አድናቆት ገልጸው፥ ኢትዮጵያ ከኮሚቴው ጋር በቅርበት ለመስራት ምንግዜም ቁርጠኛ ናት ብለዋል።
ተሰናባቹ የኮሚቴው ልዑካን መሪ ብሩስ ሎሪየንዝን በበኩላቸው፥ በቆይታቸው የመከላከያ ሚኒስቴር ለሥራቸው ላደረገው ትብብር እና ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
በቀጣይም ኮሚቴው የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ ድጋፍ የአሰራር ድንጋጌዎችን በማክበር እያከናወነች ያለውን ስራ አድንቀዋል።
በዚሁ ወቅት አዲስ የተሾሙት የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ልዑካን መሪ ሲሞኔ ካሳቢያንካ ከሚኒስትሯ ጋር ትውውቅ ማድረጋቸውን የሀገር መከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመለክታል።