በዞኑ የተገኘውን ሰላም ለማጽናት የጋራ ጥረት ማድረግ ይገባል- ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የተገኘውን ሰላም ለማጽናት የጋራ ጥረት ማድረግ ይገባል- ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 9/2017 (ኢዜአ)፡- በመዕራብ ኦሞ ዞን የተገኘውን ሰላም ለማጽናት የጋራ ትብብር እና ጥረት ማድረግ እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) ገለጹ።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) እና የማዕከላዊ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ዘውዱ በላይ በምዕራብ ኦሞ ዞን እየተከናወኑ ያሉ የፀጥታ ሥራዎችን ገምግመዋል።
በውይይቱ ላይ ከዞኑ ከተለያዩ ወረዳዎች ከተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት አድርገዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በዞኑ ከፌደራል ጀምሮ የነበረው የፀጥታ አካላትና አመራሩ ከህዝቡ ጋር በመቀናጀት በተከናወነው ሥራ የተሻለ ሰላም በአካባቢው መስፈኑን ገልጸዋል።
የተጀመረው የጋራ ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ለዘላቂነት መረጋገጥ በትኩረት እንዲሰራ አሳስበዋል።
ሌተናል ጀነራል አስራት ዲኔሮ፥ በዞኑ ሲሰሩ የነበሩና የተገኙ ውጤቶችን ያነሱ ሲሆን አመራሩ፣ህዝቡና የፀጥታ በማጠናከር አሁን የተገኘውን ውጤት ማላቅ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።
የማዕከላዊ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ዘውዱ በላይ፥ የህገ ወጥ ጦር መሳሪያ ቁጥጥርን ጨምሮ በቀጣናው የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸው፥ ለዚህም የተቀናጀ ስራ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
ጀነራል መኮንኑ ማህበረሰቡ ሰላም ለማስከበር እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) ከፌደራል እስከ ወረዳ ያለው የፀጥታ አካላትና አመራሩ በመቀናጀት በዞኑ የመጣው ሠላም ትልቅ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።
በሂደቱ የተሳተፉ እና የድርሻቸውን የተወጡ ባለድርሻ አካላትን አመስግነዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ እስከ አሁን የመጣው ውጤት ዘላቂ ለማድረግ የህግ ማስከበር ሥራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
ህገወጥ የጦር መሣሪያ ምዝገባና ቁጥጥር እንዲጠናከር፣በማዕድን አካባቢና በወረዳዎች መካከል በወሰን አካባቢ የሚስተዋሉ ችግሮችን በወንድማማችነት እና በመተጋገዝ መንፈስ መፍታት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ችግሮችን አመራሩ የፀጥታ አካላትና ህዝቡ በመቀናጀት መፍታት እንደሚገባው አመልክተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ የብልፅግና ማዕከል ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች በተቀመጠው አግባብ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አመራሩና የፀጥታ መዋቅሩ ለውጤታማነት እንዲተጋ ማሳሰባቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።