የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ አቅም እንዲጎለብት አድርጓል - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ አቅም እንዲጎለብት አድርጓል - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 9/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የተገበረችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ አቅሟ እና ተጽዕኖ ፈጣሪነቷ እንዲጎለብት ማድረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ኢትዮጵያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብሔራዊ ጥቅሟን ያስከበሩ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራዎች ማከናወኗም ተገልጿል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተሰሩ ዋና ዋና የዲፕሎማሲ ስራዎችን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሀን መግለጫ ሰጥተዋል።
ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው፤ ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ቅድሚያ በመስጠት በቀጣናው ትስስርን የሚያጠናክሩ ተግባራትን አከናውናለች ብለዋል፡፡
በውጭ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረቱ የሁለትዮሽ ግንኙነትን የሚያጠናክሩ ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውንም ገልጸዋል።
38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ እና 46ኛ የህብረቱ ሥራ አስፈፃሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ በተሳታፊዎች ዘንድ አድናቆት የተቸረው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ውጤታማ ሥራዎችን ከማከናወን ባለፈ ለ968 ዜጎች ነፃ የትምህርት እድል ማመቻቸት እንደተቻለም ገልጸዋል፡፡
በሁለትዮሽ ዲፕሎማሲ ከተለያዩ ሀገራት ጋር 11 ስምምነቶች ተፈርመው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው እንዲጸድቁ መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ከሀምሌ ወር 2016 ዓ.ም ጀምሮ ገቢራዊ የተደረገው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የሀገሪቱን የዲፕሎማሲ አቅምና ተጽዕኖ ፈጣሪነት እንዲጎለብት ማስቻሉን ገልጸዋል፡፡
በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማሻሻል በሚሲዮኖች በኩል 143 የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት እድሎች የማስተዋወቅ ሥራ ተሰርቷል ብለዋል፡፡
በዚሀም 533 ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የቅድመ ኢንቨስትመንት ጉብኝት ማድረጋቸውን ገልጸው፤ የኢትዮጵያን ምርቶች በ88 የንግድ ማስተዋወቂያ መድረኮች በመሳተፍ 98 አዳዲስ የገበያ ትስስር መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡
በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ስራዎች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ከ92ሺህ በላይ ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅትም በማይናማር በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ 700 የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ለመመለስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በቅርቡ ከ130 በላይ ኢትዮጵያውያን ከማይናማር መመለሳቸውን ገልጸው፤ በቀጣዮቹ አስር ቀናትም 200 ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ለማድርግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡