ለቀድሞ ታጣቂዎች የሚሰጠው የተሀድሶ ስልጠና ለዘላቂ ሰላም ግንባታ አዎንታዊ ሚና እየተወጣ ነው - ብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
ለቀድሞ ታጣቂዎች የሚሰጠው የተሀድሶ ስልጠና ለዘላቂ ሰላም ግንባታ አዎንታዊ ሚና እየተወጣ ነው - ብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 9/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ለቀድሞ ታጣቂዎች የሚሰጠው የተሀድሶ ስልጠና ለዘላቂ ሰላም ግንባታ አዎንታዊ ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ ብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን ገለጸ።
በአገር ደረጃ በአፋር፣ ትግራይ፣ አማራና ኦሮሚያ ክልሎች 25 ሺህ የቀድሞ ታጣቂዎች በተሀድሶና መልሶ ማቋቋም ስልጠና ሂደት ማለፋቸውም ተገልጿል።
በትግራይ ክልል ተቋርጦ የቆየው የቀድሞ ታጣቂዎች የተሀድሶና መልሶ ማቋቋም ስልጠና ዛሬ ዳግም ተጀምሯል።
የስልጠና ሂደቱንም የአፍሪካ ሕብረትና የዓለም አቀፍ ተቋማት ታዛቢዎች ልዑክ በመቀሌ የስልጠና ማዕከል ተገኝተው ምልከታ አድርገዋል።
የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ከትግራይ ክልል በተጨማሪም በአፋር፣ አማራና ኦሮሚያ ክልሎችም የቀድሞ ታጣቂዎችን በተሀድሶ ስልጠና በማሳለፍ ወደ ማህበረሰቡ የመቀላቀል ስራ ተከናውኗል።
በትግራይ ክልል ቀደም ሲል ስልጠና ሲሰጥባቸው በቆዩት የመቀሌና ዕዳጋ ሀሙስ የተሀድሶና መልሶ ማቋቋም የስልጠና ማዕከላት የቀድሞ ታጣቂዎችን ተቀብለው እያስተናገዱ እንደሚገኙም አስታውቀዋል።
አሁን ላይ አምስት ሺህ የቀድሞ ታጣቂዎች በተሀድሶ ስልጠና እያለፉ ይገኛሉ ያሉት ኮሚሽነሩ፤ በእስከ አሁኑ ሂደት 12 ሺህ የሚጠጉ የትግራይ ክልል የቀድሞ ታጣቂዎች በተሀድሶና መልሶ ማቋቋም ስልጠና እንዲያልፉ መደረጉን አስታውቀዋል።
በአጠቃላይ እንደ አገር በአፋር፣ ትግራይ፣ አማራና ኦሮሚያ ክልሎች 25 ሺህ የቀድሞ ታጣቂዎች በተሀድሶና መልሶ ማቋቋም ስልጠና ሂደት ማለፋቸውን አብራርተዋል።
የተሀድሶ ስልጠናውም በዘላቂ ሀገራዊ ሰላም ግንባታ አዎንታዊ ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ትጥቅ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን በመቀበል በተሀድሶ ስልጠና መደበኛ ህይወታቸውን መምራት እንደሚኖርባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።
በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ፍስሀ ኪዳኑ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መነሻነት የተቀመጡ አቅጣጫዎችን ለመፈጸም በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው።
የቀድሞ ታጣቂዎችን በተሀድሶ ስልጠና ወደ ማህበረሰቡ በመቀላቀል መደበኛ ህይወታቸውን እንዲመሩ የማድረግ ስራም በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ሳሙኤ ገባይዴ ዶ በመቀሌ የስልጠና ማዕከል የቀድሞ ታጣቂዎች የዲሞብላይዜሽንና መልሶ ማቋቋም የስልጠና ሂደት በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ እንደሚገኝ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይም የቀድሞ ታጣቂዎችን የተሀድሶ ስልጠና ሂደት የመንግስታቱ ድርጅት የልማት ተቋማት የሚያደርጉት ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በምልከታው በአፍሪካ ሕብረት የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት የቁጥጥር፣ ማረጋገጥና ማስከበር ተልዕኮ ልዑክ ኃላፊ ሜጀር ጄኔራል ሳማድ አላዴ፣ አሕጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የአጋር የልማት ድርጅቶችና የሀገራት ተወካዮች ተገኝተዋል።