ተለዋዋጭ በሆነው የዓለም ሁኔታ የሚፈጠሩ ዕድሎችን በአግባቡ ለመጠቀም ይበልጥ መስራት ይገባል - ሚኒስትር አብርሃም በላይ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ተለዋዋጭ በሆነው የዓለም ሁኔታ የሚፈጠሩ ዕድሎችን በአግባቡ ለመጠቀም ይበልጥ መስራት ይገባል - ሚኒስትር አብርሃም በላይ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 9/2017(ኢዜአ)፦ ተለዋዋጭ በሆነው የዓለም ሁኔታ የሚፈጠሩ ዕድሎችን በአግባቡ ለመጠቀም ይበልጥ መስራት እንደሚገባ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር አብርሃም በላይ(ዶ/ር) ገለጹ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት ሰራተኞች እና አመራሮች በ2017ዓ.ም የዘጠኝ ወራት ሀገራዊ እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ ውይይት አድርገዋል።
በመድረኩ የአፈፃፀም ሪፓርቱን ያቀረቡት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍፁም አረጋ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የነበረው የማክሮ ኢኮኖሚ አፈፃፀም ምርታማነትን እና ተወዳዳሪነትን ማሳደግ ያስቻለ ነው ብለዋል።
በ2017ዓ.ም ዘጠኝ ወራት ኢኮኖሚው በ8 ነጥብ 4 በመቶ ማደጉ የተገለፀ ሲሆን 5 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ከወጪ ንግድ መገኘቱን ገልጸዋል።
በዲኘሎማሲ መስክ የሁለትዮሽ ግንኙነትን በማጠናከር እንዲሁም በባለብዙ ወገን መድረኮች ኢትዮጵያ ተሳትፎዋን ማሳደግ እና ጥቅሞቿን ማስጠበቅ ያስቻሉ ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውን አምባሳደር ፍፁም አንስተዋል።
በዘጠኝ ወሩ በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሬሚታንስ ከ3 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር በላይ ገንዘብ ወደ ሀገር ውስጥ የተላከ ሲሆን ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 12 በመቶ እድገት እንዳለው ገልጸዋል።
መድረኩን በአወያይነት የመሩት የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ(ዶ/ር) እንዳሉት ውይይቱ ሀገራችን ያለችበትን ሁኔታ እና እየሄደችበት ያለውን መንገድ ለመገንዘብ የሚያስችል ነው።
ባለፉት ሰባት አመታት የተተገበሩ ሁለንተናዊ የሪፎርም ስራዎች የኢትዮጵያን የእድገት ማነቆዎች ለመፍታት እና ሉዐላዊነትን ለማረጋገጥ ያስቻሉ እንደሆነ ተናግረዋል።
የአለም ሁኔታ ተለዋዋጭነት እየጨመረ መምጣቱን ገልጸው በመጪው ጊዜ የሚፈጠሩ እድል እና ስጋቶችን በጥልቀት በመመዘን ጥቅማችንን ለማሳደግ መስራት አለብን ብለዋል።
በተለይ በአሁኑ ወቅት ያለው የታሪፍ ጦርነት በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ እና የንግድ ስርአት ላይ የሚያመጣውን ተጽዕኖ በማጤን በቀጣይ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስከብሩ እርምጃዎች ሊወሰዱ እንደሚገባ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ በምትገኝበት ቀጣና ለሰላም እና መረጋጋት ወሳኝ ሚና የምትጫወት መሆኗን ዳግም ያረጋገጠችባቸው ስኬቶች ባለፉት ዘጠኝ ወራት መመዝገባቸው በውይይቱ ላይ ተመላክቷል።