የባህር ኃይል ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተፋጠነ ነው- ሬር አድሚራል ክንዱ ገዙ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 9/2017 (ኢዜአ)፦ የባህር ኃይል ፕሮጀክቶች ግንባታ በተፋጠነ መልኩ እየተሰራ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ባህር ኃይል ዋና አዛዥ ሬር አድሚራል ክንዱ ገዙ ገለጹ።

ዋና አዛዥ ሬር አድሚራል ክንዱ ገዙ ከክፍሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን እየተገነባ ያለውን የባህር ኃይል ጠቅላይ መምሪያና የባህር ኃይል መሠረታዊ ባህረኞች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የግንባታ ሂደት ተመልክተዋል፡፡

የቢሾፍቱ ባህረኞች ትምህርት ቤት የግንባታ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኮሎኔል ኢንጂነር መሀመድ ሀሰን የባህር ኃይል የባህረኞች ትምህርት ቤት ግንባታ በተያዘለት ጊዜ አጠናቆ ለማስረከብ 24 ሰዓት በትጋት እየተሰራ ነው ብለዋል።


 

በተመሳሳይ አዲስ አበባ ጃንሜዳ የሚገነባው የኢትዮጵያ ባህር ኃይል ጠቅላይ መምሪያ ግንባታ ፕሮጀክት ኃላፊ ሌተናል ኮሎኔል ኢንጂነር በቀለ መለሰ የጠቅላይ መምሪያው ቢሮዎች፤ የህክምና አገልግሎት መስጫ ክሊኒክ፤ የስብሰባ አዳራሽ፤ ስቶር፤ የስፖርት ማዘውተሪያ መሠረተ ልማትና ሌሎች አገልግሎቶችን ግንባታ በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል።

ለፕሮጀክቱ ጥራት እና ፍጥነት የአመራሩ ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን አመልክተዋል።


 

የኢትዮጵያ ባህር ኃይል ዋና አዛዥ ሬር አድሚራል ክንዱ ገዙ ባህር ኃይሉን ለማጠናከር በመንግስት አስፈላጊው በጀት መመደቡንና በከፍተኛ አመራሩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ዋና አዛዡ የፕሮጀክቶቹ ግንባታ በጥሩ ደረጃ እና በተፈለገው ፍጥነት እየሄደ እንደሚገኝ መግለጻቸውን የሀገር መከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም