መንግስት የዲሞክራሲ ስርዓትን የሚያጠናክሩ ተቋማት ግንባታ ላይ አበክሮ እየሰራ ነው - የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጂጌ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 9/2017(ኢዜአ)፦ መንግስት የዲሞክራሲ ስርዓትን የሚያጠናክሩ ተቋማት ግንባታ ላይ አበክሮ እየሰራ መሆኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጂጌ(ዶ/ር) ገለጹ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው የመገናኛ ብዙሃን አዋጅን ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጂጌ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ባለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታት መንግስት ሀገርንና ሕዝብን የሚያገለግሉ ነጻ፣ ገለልተኛ እና ብቁ ተቋማትን መፍጠር የሚያስችሉ ተግባራትን አከናውኗል።


 

የዲሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ላይ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመው፤ በዚህም የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታን የሚያጠናክሩ እንደ መገናኛ ብዙሃን ያሉ ተቋማትን አቅም የመገንባት ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።

ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ህገ መንግስታዊ መሆኑን ገልጸው በዚህም መገናኛ ብዙሃን ነጻነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ በዘርፍ የሚታዩ ተጨባጭ ውጤቶች መገኘታቸውን ጠቁመዋል።

በመሆኑም የሕዝብ፣ የግል እና የሃይማኖት መገናኛ ብዙሃን በብዛት፣ በቋንቋ እንዲሁም በስርጭት ቁጥራቸው በእጅጉ መጨመሩን ተናግረዋል።

ነገር ግን የሃሳብ ነፃነት ባልተገባ መንገድ ሲገለፅና ከህግ ወጪ ሲሆን ደግሞ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ አስፋለጊ እንደሆነም ገልጸዋል።


 

የመገናኛ ብዙሃን አዋጅን ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አስመልክቶ የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቱ አለነ ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ አቅርበዋል።

በስራ ላይ የነበረው የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ከአፈጻጸም ጋር በተያያዘ የአደረጃጀት፣ የቁጥጥር መላላትና ከአስተዳደር ጋር ክፍተቶች ያሉበት በመሆኑ ማሻሻያ እንደተደረገበት ገልጸዋል።

የባለሥልጣኑ የዕለት ተዕለት ሥራዎች አፈጻጸም፣ የቦርድ አሰያየም፣ የቁጥጥር እና ተጠያቂነት ስርዓት ጋር በተያያዘ ክፍተቶች ያሉበት በመሆኑ መሻሻል ማስፈለጉን ተናግረዋል።

የተሻሻለው አዋጅ መገናኛ ብዙሃን እንዲጠናከሩና ተወዳዳሪ ሆነው እንዲቀጥሉ እንዲሁም በቴክኖሎጂ እየዘመኑ እንዲሄዱ የሚያደርግ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዘርፉ ያሉ ክፍተቶችን በማስተካከል መገናኛ ብዙሃንን በአግባቡ ማስተዳደር እና መቆጣጠር እንዲቻልም የመገናኛ ብዙሃን አዋጅን ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱ ጠቁመዋል።

የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው የተሻሻላው አዋጅ ለመገናኛ ብዙሃን ምቹ ምህዳር የሚፈጥር በመሆኑ የሚዲያ ነጻነት እንዲተገበር ያግዛል ብለዋል።

በተጨማሪም ከሕግ አግባብ ውጪ በሚንቀሳቀሱት ላይ በሀገሪቱ ሕግ መሰረት እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባም ገልጸዋል።


 

በተመሳሳይ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ማስፈጸሚያ የተፋሰሶች ከፍተኛ ምክር ቤት ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅን አስመልክቶ የውሃ፣ መስኖና ቆላማ አካባቢዎች እና አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ፈቲያ አህመድ ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ አቅርበዋል።

ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም