ማንችስተር ዩናይትድ ሊዮንን ድራማዊ በሆነ ሁኔታ በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍጻሜ አለፈ 

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 9/2017 (ኢዜአ)፦ በዩሮፓ ሊግ ሩብ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታ ማንችስተር ዩናይትድ ሊዮንን 5 ለ 4 አሸንፏል።

ማምሻውን በኦልድትራፎርድ ስታዲየም የተደረገው ጨዋታ በልብ አንጠልጣይ ክስተቶች የታጀበ ነበር።

ማኑኤል ኡጋርቴ እና ዲዮጎ ዳሎት በመጀመሪያ አጋማሽ ባስቆጠሯቸው ጎሎች ማንችስተር ዩናይትድ 2 ለ 0 መምራት ችሏል::

ኮረንቲን ቶሊሶ እና ኒኮላስ ታግሊያፊኮ ከእረፍት መልስ ከመረብ ላይ ያሳረፏቸው  ግቦች ሊዮንን አቻ አድርገዋል።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሁለት አቻ በመጠናቀቁ ወደ ጭማሪ 30 ደቂቃ አምርቷል።

ራያን ቼርኪ በ105ኛው በጨዋታ እና አሌክሳንደር ላካዜት በ110ኛው ደቂቃ በፍጹም ቅጣት ያስቆጠሯቸው ጎሎች ግብ ሊዮንን 4 ለ 2 መሪ አድርጎ ነበር።

ይሁንና ብሩኖ ፈርናንዴዝ በ114ኛው ደቂቃ በፍጹም ቅጣት ምት፣ ኮቢ ሜይኖ በ120ኛው እና ሀሪ ማጓየር በ121ኛው ደቂቃ  ያስቆጠሯቸው ግቦች ለማንችስተር ዩናይትድ ጣፋጭ ድል አስገኝቷል።

የሊዮኑ ኮረንቲን ቶሊሶ በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።

ውጤቱን ተከትሎ ማንችስተር ዩናይትድ በድምር ውጤት 7 ለ 6 በማሸነፍ ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል።

ማንችስተር ዩናይትድ በግማሽ ፍጻሜው ከአትሌቲኮ ቢልባኦ ጋር ይጫወታል።

አትሌቲኮ ቢልባኦ ሬንጀርስን በደርሶ መልስ ውጤት 2 ለ 0 በማሸነፍ ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል።

በሌሎች ጨዋታዎች  ቶተንሃም ሆትስፐርስ ኢንትራክት ፍራንክፈርትን፣  ቦዶ ግሊምት ላዚዮን በድምር ውጤት በማሸነፍ ለግማሽ ፍጻሜ አልፈዋል።

ቶተንሃም ሆትስፐርስ እና ቦዶ ግሊምት በግማሽ ፍጻሜው ይገናኛሉ።

የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች በሚያዚያ ወር መጨረሻ ይካሄዳሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም