ኢትዮጵያ እና ቬይትናም ትብብራቸውን የሚያጠናክሩ ስምምነቶችን አድርገዋል - ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 10/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ቬይትናም ትብብራቸውን የሚያጠናክሩ ስምምነቶች ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ እና ቬይትናም ግንኙነት 50 ዓመታትን ማስቆጠሩን ያነሱት ሚኒስትሩ፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በቬይትናም ያደረጉት ጉብኝት በሀገራችን ታሪክ የመጀመሪያው የመሪ ጉብኝት መሆኑን ተናግረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የልዑካቸው የቬይትናም ጉብኝት ስኬታማ እንደሆነ በማውሳት፥ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ሰፊ ውይይት ማድረጋቸውን ተከትሎ ትብብርን የሚያጠናክሩ የተለያዩ ስምምነቶች መፈረማቸውን ጠቅሰዋል።


 

ከስምምነቶቹ መካከል የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቬይትናም በረራ እንዲጀምር የሚያስችለው ተጠቃሽ መሆኑን ጠቁመው፤ አየር መንገዱ በረራ ሲጀምር የሀገራቱን የንግድ ግንኙነት፣ የህዝብ ለህዝብና የኢኮኖሚ ትስስር ያጠናክራል ብለዋል።

በትምህርት ዘርፍ፣ በኢኮኖሚ፣ በንግድ እና በኢንቨስትመንት ግንኙነትን የሚያጠናክሩ ስምምነቶች መደረጋቸውንም አስረድተዋል።

በቀጣይም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ምን ዓይነት የትብብር ማዕቀፍ መከተል እንደሚያስፈልግ ስምምነት ለማድረግ ውይይት መደረጉንም ጠቅሰዋል።

ይህ እውን ሲሆን ተቋማዊና ዘላቂ የሆነ ሁለቱንም ሀገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ ጠንካራ ግንኙነት እንዲኖር ያስችላል ነው ያሉት።


 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አክለውም ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ልማት ትብብር(ፒ4ጂ) በ2027 የሚያደርገውን ዓለም አቀፍ ጉባዔ እንድታስተናግድ መመረጧንም አንስተዋል።

ዓለም አቀፍ የትብብር መድረኩ ኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይልና የአረንጓዴ ልማት ሥራዎቿን ለዓለም እንድታሳይ ትልቅ እድል መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ የታዳሽ ኃይል እንደምትጠቀም አመልክተው፤ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ፈሰስ በማድረግ የታዳሽ ኃይል ልማት እያከናወነች እንደምትገኝ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።

በዘላቂነት በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ብቻ ለመጠቀም ግልጽ አቋም ይዛ እየሰራች መሆኗንም ገልጸዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርም ከራሷ አልፎ ለዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ መቋቋም ሥራዎች አጋዥና ምሳሌ እንደሆነም ጠቁመዋል።


 

የፒ4ጂ የትብብር መድረክን ለማዘጋጀት መመረጧም ተፅዕኖ ፈጣሪነቷ እና ተሰሚነቷ እያደገ መምጣቱን ማሳያ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

መድረኩ የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ልማት ተነሳሽነቶችና ተግባራዊ ስራዎችን ሌሎች ሀገራት በመመልከት በጋራ የመስራት አቋም እንዲወስዱ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።

በአካባቢ ጥበቃና ዘላቂ ልማት ላይ መንግሥታት ብቻ ሳይሆኑ የግሉ ዘርፍ በቂ ፋይናንስ በማሰባሰብ ሚናውን እንዲወጣ የማድረግ ዓላማ እንዳለውም ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም