ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና እና የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሰራች ነው- አምባሳደር ልዑልሰገድ ታደሰ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 10/2017 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ የግብርና ፕሮግራሞችን በመተግበር የምግብ ዋስትና እና የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሰራች እንደምትገኝ በብራዚል የኢትዮጵያ አምባሳደር ልዑልሰገድ ታደሰ ገለጹ።

ኢትዮጵያ በብራዚል መዲና ብራዚሊያ በተካሄደው የብሪክስ የግብርና ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ተሳትፋለች።

ብሪክስ ፍትኃዊና ወካይ የዓለም ሥርዓት ለመፍጠር ከፍተኛ ሚና ያበረክታል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

በብራዚል የኢትዮጵያ አምባሳደር ልዑልሰገድ ታደሰ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) አመራር ሰጪነት እየተተገበሩ ያሉ ዘርፈ ብዙ የተቀናጁ ፖሊሲዎች እና ኢንሼቲቮችን አስመልክቶ ለስብሰባው ተሳታፊዎች ገለጻ አድርገዋል።


 

የስንዴ ልማት፣ አረንጓዴ አሻራ፣ የሌማት ትሩፋት፣ ኩታገጠም እርሻ፣ የተጎዳ መሬት መልሶ ማልማት እና የመስኖ ኢኒሼቲቮችን ለአብነት አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ያስመዘገበቻቸው ስኬቶች ጠንካራ የፖለቲካ ቁርጠኝነት፣ አመራር እና የተቀናጁ ኢኒሼቲቮች አፍሪካን መለወጥ እንደሚችሉ ማሳያ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ የግብርና ፕሮግራሞችን በመተግበር የምግብ ዋስትና እና ሉዓላዊነትቷን ለማረጋገጥ አበክራ እየሰራች እንደምትገኝ አመልክተዋል።

በዚህ ረገድም ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባል እና አጋር አገራት ጋር በመሆን በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የእውቀት ማጋራት እና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗንም ተናግረዋል።

አምባሳደር ልዑልሰገድ በኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ ስላሉ መጠነ ሰፊ የግብርና እድሎች ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን የብሪክስ የንግድ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ በዘርፉ  ያሉ አማራጮችን በመቃኘት በኢንቨስትመንት መስክ እንዲሰማራ ጥራ አቅርበዋል።

ከግብርና ሚኒስትሮች ስብሰባ አስቀድሞ የግብርና ከፍተኛ አመራሮች ስብሰባ መካሄዱን በብራዚሊያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም