የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቬይትናም ጉብኝት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተሰሚነት ከፍ ያደረገ ነው - አምባሳደር ደሴ ዳልኬ - ኢዜአ አማርኛ
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቬይትናም ጉብኝት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተሰሚነት ከፍ ያደረገ ነው - አምባሳደር ደሴ ዳልኬ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 10/2017(ኢዜአ)፦ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የቬይትናም ጉብኝት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተሰሚነት የሚያሳድግ አጋርነት የተፈጠረበት መሆኑን በኮሪያ ሪፐብሊክ የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሴ ዳልኬ ገለጹ፡፡
በኮሪያ ሪፐብሊክ የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሴ ዳልኬ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የቬይትናም ጉብኝትን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያቸውም በኢትዮጵያ እና ቬይትናም መካከል መደበኛ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጀመረው እ.አ.አ በ1976 መሆኑን ጠቅሰዋል።
ቬይትናም እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ በመርህ ላይ የተመሰረተ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የምትከተል ሀገር መሆኗን ገልጸው፤ በአየር ንብረት እና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ተመሳሳይ አቋም ያላቸው መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ልዑካቸው በቬይትናም ቆይታቸው ከተለያዩ የሀገሪቱ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ጠቅሰው፤ ውይይቱ በሁለትዮሽ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት እድል የሚፈጥር መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያ እና ቬይትናም በዓለም አቀፍ እና ሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ በትብብር መስራት በሚችሉበት ጉዳይ ላይ ውይይት ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቬይትናም ደግሞ በኤዥያ ግዙፍ ኢኮኖሚ እየፈጠሩ ያሉ ሀገራት መሆናቸውን ገልጸው፤ ይህም ሁለቱ ሀገራት እርስ በእርስ የገበያ እድል እንዲፈጥሩና ልምድ እንዲለዋወጡ ያስችላቸዋል ነው ያሉት፡፡
ቬይትናም በአምራች ኢንዱስትሪ ጨርቃ ጨርቅ፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶችን እንዲሁም የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን ለውጭ ገበያ የምታቀርብ መሆኗ ልምድ የሚወሰድበት መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል፡፡
ቬይትናም የዓለም ሁለተኛዋ ኢትዮጵያ ደግሞ ሶስተኛዋ ቡና አምራች ሀገሮች መሆናቸውን ገልጸው፤ ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥ ሥምምነት ላይ መድረሳቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በስምምነቱ ላይ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃ ዝርዝር አፈፃፀም ሂደቱን የሚከታተል አካል ለመሰየም መነጋገራቸውንም አምባሳደር ደሴ ገልጸዋል፡፡
ቬይትናምና ኢትዮጵያ ወደ አፍሪካና ወደ ኤዥያ መግቢያ በር እና አገናኝ ድልድይ ሆነው እንደሚያገለግሉ ጠቅሰው፥ ይህም ከሁለቱ ሀገራት ያለፈ ፋይዳ እንዳለው አስረድተዋል።