የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም የጋራ አመራር እና አስቸኳይ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም የጋራ አመራር እና አስቸኳይ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 10/2017(ኢዜአ)፦ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም የጋራ አመራር እና አስቸኳይ እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) “ዘላቂ እና ሕዝብን ማዕከል ያደረገ አረንጓዴ ሽግግር” በሚል መሪ ሀሳብ በተካሄደው የ2025 ፒ4ጂ ቬይትናም ጉባኤ ተሳትፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል እና ይህን ጠቃሚ ጉባኤ ላዘጋጀው የቬይትናም መንግስት ምስጋና በማቅረብ በአየር ንብረት ለውጥና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የ2025 ፒ4ጂ ጉባዔ የአረንጓዴ ልማት እድገትን ለማፋጠን፣ አዳዲስ አጋርነቶችን ለማጎልበት እና የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ለሚደረገው የጋራ ቁርጠኝነት ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፉት ጥቂት ቀናት የአንድነትና የብዝሃነት ሃይል ማሳካት የሚችለውን አቅም አይተናል ብለዋል።
የተቀናጁ የፒ4ጂ ፕሮጀክቶች ትርጉም ያለው ውጤት የሚያስገኙና ይህን ለማሳደግም ትልቅ አቅም ያላቸው መሆናቸውን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በ2027 የሚካሄደውን አምስተኛውን የፒ4ጂ ጉባኤ ለማዘጋጀት ችቦውን በመረከቧ ኩራት እንደሚሰማት ገልጸዋል።
ይኽን እድል በፅናት እና በቁርጠኝነት በመያዝ የቬይትናም፣ ኮሎምቢያ፣ ዴንማርክ እና የኮሪያ ሪፐብሊክን ስኬታማ የዝግጅት ውርስ ጨምረን እናስቀጥላለን ሲሉም ተናግረዋል።
ጉባኤው ትብብር፣ ፈጠራ፣ አካታችነት እና ተግባር በተሰኙት የፒ4ጂ አስኳል መርሆዎች እየተመራ እንደሚካሄድም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ 2027 ጉባኤ በአረንጓዴ ኢንዱስትሪ ልማት፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ግብርና እንዲሁም ወጣቶችንና ሴቶችን ማብቃትን የአረንጓዴ ሽግግር ወሳኝ መሳሪያ የማድረግ አስፈላጊነትን ትኩረት ሰጥቶ እንደሚዘጋጅ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ ከሆኑ ሀገራት ተርታ መሆኗን አመልክተው፤ ይህንን ለመፍታት የተግባር ቁርጠኝነቷን እያሳየች ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከአጀንዳ 2030 እና ከአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 ጋር በተጣጣመ መልኩ እ.አ.አ በ2050 ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ስርዓት እውን የማድረግ ትልቅ ትልም ማዘጋጀቷን ተናግረዋል።
ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር እና እየተስፋፋ ያለው የታዳሽ ሃይል ልማት ለዚህ ራዕይ ያለንን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።
ይሁን እንጂ የትኛውም ሀገር የአየር ንብረት ቀውስን ብቻውን መቋቋም እንደማይችል አመላክተዋል።
ይህንን ችግር የመፍቻ መንገዱ የጋራ አመራር እና አስቸኳይ እርምጃን የሚጠይቅ መሆኑንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የፒ4ጂ በ2018 ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ለመድረኩ አስተዋፅዖ ማበርከቷን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል።
በምግብ ሥርዓት፣ በታዳሽ ኃይል፣ ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ የማይበገሩ ከተሞች እና በኢኮኖሚ ውስጥ ባሉ የትብብር ፕሮጀክቶች አብረን ስንሠራ የሚቻለውን አይተናል ሲሉም ተናግረዋል።
እንደ ፒ4ጂ መስራች አባልነቷ፥ ቁልፍ የአየር ንብረት ስምምነቶች፣ ኢትዮጵያ አረንጓዴ ማገገምን እና ዘላቂ ልማትን ለማራመድ ቁርጠኝነቷን እንደምታስቀጥልም ነው ያስረዱት።
በዚህ አውድም፥ በቬይትናም መንግስት የቀረበውን የሃኖይ ዲክላሬሽን ሙሉ በሙሉ እንደሚደግፉ አረጋግጠዋል።
የቬይትናም መንግስት ይህንን ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ በማዘጋጀቱ፣ ለአረንጓዴና የበለጠ አካታች ዓለም ላበረከቱት አስተዋፅዖ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።
ቀደምት የሰው ዘርና የቡና መገኛዋን እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በዓለም ትልቁ የደን ልማት መርሃ ግብር እየተገበረች ያለችውን ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ ለጉባኤው ተሳታፊዎች ጥሪ አቅርበዋል።