ኢትዮጵያ በስኬት ጉዞዋ እጅግ አስፈላጊ አገር እየሆነች ነው- ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 10/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በጂኦፖለቲካል ነባራዊ ሁኔታና መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ብቻ ሳይሆን ከአሁናዊ የብልፅግና እይታና ፕራግማቲክ ጉዞዋ የሚቀዳ የስኬት ጉዞዋ እጅግ አስፈላጊ አገር እየሆነች ነው ሲሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር) ገለጹ።

ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የቬይትናም ጉብኝት ኢትዮጵያ እጅግ አስፈላጊ አገር መሆኗን ያረጋገጠ ቆይታ ሲሉም ገልጸዋል።

የሚኒስትሩ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፦

ኢትዮጵያ እጅግ አስፈላጊ አገር መሆኗን ያረጋገጠ ቆይታ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ከልዑካን ቡድናቸው ጋር በቬየትናም የነበራቸው ይፋዊ ጉብኝት የተሳካና ኢትዮጵያ እጅግ አስፈላጊ አገር መሆኗን ያረጋገጠ ነው። ኢትዮጵያ በጂኦፖለቲካል ነባራዊ ሁኔታና መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ብቻ ሳይሆን ከአሁናዊ የብልፅግና እይታና ፕራግማቲክ ጉዞዋ የሚቀዳ የስኬት ጉዞዋ እጅግ አስፈላጊ አገር እየሆነች ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ በያዝነው ሳምንት ለይፋዊ መንግስታዊ ጉብኝት ወደ ቬትናም  አቅንተው ነበር። ጉብኝታቸው በሁለቱ ሀገሮች መካከል ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከተጀመረበት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 1976 ወዲህ በሀገር መሪ ደረጃ ሲደረግ የመጀመሪያው ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ላለፉት 50 ዓመት ያህል በመሪዎች ደረጃ ያልነበረውን ግንኙነት የቀየረ እጥፋት ሆኗል። በዚህም ምክንያት ቬየትናም በመሪዋ ለጠቅላይ ሚኒስትራችን ይህን የቆየ ወዳጅነትና ስትራቴጂክ አጋርነትን የሚያጠናክር፣ የመሪያችንንና የህዝባቸውን ክብር የሚመጥን እጅግ የደመቀ አቀባበል አድርጋላቸዋለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ በቆይታቸው ከሀገሪቱ ፕሬዚደንት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የብሄራዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት እና የሀገሪቱ ገዥ ፓርቲ ከሆነው የቬየትናም ኮሚኒስት ፓርቲ ዋና ፀሐፊ ጋር በሁለትዮሽ፣ ቀጠናዊ እና አለም አቀፋዊ ጉዳዮች እንዲሁም ብዝሃ ግንኙነቶች ላይ ያተኮረ የሰከነ እና ጥልቀት ያላቸው ውይይቶችን አድርገዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር / ዐቢይ እና ልዑካቸው፣ ከሀገሪቱ ቁልፍ የአምራች ኢንዱስትሪ ባለቤቶች ጋርም የመወያየት እድል አግኝቷል፡፡ የሮቦቲክ እና ሃይቴክ ኢንዱስትሪዎችንም ጎብኝቷል፡፡ ኦሽን ፓርክ በመባል የሚታወቀውን በሀገር በቀል ኩባንያ የሚለማ የከተማ ግንባታ ስራዎችንም ተመልክቷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩና ልዑካቸዉ በሁለትዮሽ እና ብዝሃ ግንኙነቶች ላይ ያተኮሩ ውይይቶችን ከማድረጋቸውም በላይ በንግድ እና ኢንቨስትመንት፣ በሰው ሀብት ልማት እና አቪዬሽን ኢንደስትሪ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የጋራ የመግባቢያ ስምምነቶች ፈርመዋል፡፡ ከእነዚህም በተጨማሪ ልዑኩ፣ አጋርነት ለዕድገት እና ልማት (P4G) ዓለም አቀፍ ጉባዔ ላይ በመገኘት የኢትዮጵያን ልምድና ተሞክሮ አካፍሏል፡፡

የደቡብ ምስራቅ እስያ አካል የሆነችው ቬየትናም ከቀጠናው አገሮች እጅግ በመዘግየት ማለትም 1986 በሯን ለዓለም የከፈተችና የኢኮኖሚ ሪፎርሟን የጀመረች አገር ናት፡፡ ለሀገራዊ አንድነትና ብሔራዊ ጥቅም፣ የተረጋጋ ኢኮኖሚና ፈጣን እድገት ልዩ ትኩረት የሚሰጠው የኢኮኖሚ ሪፎርሟ ዶይ ሞይ (Đổi Mới) ወይም Economic renovation through opening up በመባል የሚታወቅ ነው፡፡

ቬየትናም የኢኮኖሚ ሪፎርሙን መሠረት በማድረግ በጠንካራ ፓርቲ የሚመራ ጠንካራ መንግስት በመገንባቷ ባለፉት 30 ዓመታት እጅግ አስደናቂ የሚባል የኢኮኖሚ እድገትና ማህበራዊ ለውጥ ያስመዘገበች ሀገር ናት፡፡ 1990ዎቹ በፊት እጅግ ደሃ ከሚባሉ ሀገሮች ታርታ ተሰላፊ የነበረች ሲሆን፣ ከነበረችበት እጅግ ጥልቅ የሆነ ድህነት ተነስታ በአንድ ትውልድ ብቻ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ መሰለፍ የቻለች ሀገር ናት፡፡

ቬየትናም ዛሬ በምግብ ሰብል ራሷን ከመቻል አልፋ በቀጠናው በግብርና ምርቶች በተለይም በሩዝ፣ በቡና፣ ፍራፍሬና ሌሎች ምርቶች ግምባር ቀደም ላኪ ሀገር መሆን ችላለች፡፡ የከፍተኛ አምራች ኢንደስትሪ ማዕከል (Industry Hub) በመፍጠር በከፍተኛ ቴክኖሎጂ የሚታገዙ የኤሌክትሮኒክስ፣ የጨርቃ ጨርቅ እና የመጫሚያ ምርቶችን በከፍተኛ ደረጃ ኤክስፖርት ከሚያደርጉ አገሮች ተርታ የምትሰለፍ ናት፡፡

በጠንካራ ፓርቲ የሚመራው የቬየትናም ጠንካራ መንግስታዊ ቢሮክራሲ፣ ለብዝሃ የኢኮኖሚ ግንባታ በተለይም ለግብርና ልማት እና ኤክስፖርት መር አምራች ኢንዱስትሪዋ ስኬታማነት የላቀ አበርክቶ አለው፤ ሀገሪቱ በዚህ እይታ በአለም አቀፍ ደረጃና በቀጠናው ለነጻ የንግድ ስምምነቶች እና ዝቅተኛ ታሪፍ እንዲሁም በክህሎትና እውቀቱ የበለፀገ የሰው ኃይል ልማት የሰጠችው ትኩረት ለኢኮኖሚ እድገቷና ልማቷ ውጤታማነት መሰረት ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡

የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ይፋዊ ጉብኝትም ሀገራችን የጀመረችውን የማህበረ-ኢኮኖሚያዊ የሪፎርም ስራዎችን የሚያጠናክሩ፣ የሁለቱን ሀገሮች ስትራቴጂካዊ አጋርነት የሚያጎለብቱ፣ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን የሚያሳልጡ ልምዶች መቅሰም አስችሏል፡፡ የተገኙ ልምዶችና ተሞክሮዎችንም ከብዙ በጥቂቱ እንደሚከተለው ማስቀመጥ ይቻላል፡፡

ተሞክሮ አንድ፣

ለብዝሃ የኢኮኖሚ ግንባታ ትኩረት በመስጠትና በፅናት የታገዘ እልህ አስጨራሽ ርብርብ በማድረግ በአንድ ትውልድ የጊዜ ምዕራፍ ውስጥ ብቻ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት መዝገብ የሚቻል መሆኑን ከቬየትናም የኢኮኖሚ ልማት አቅጣጫ መረዳት ይቻላል፡፡ ቬየትናሞች ለግብርና ልማት፣ አምራች  ኢንዱስትሪ፣ ለቱሪዝም፣ ለሰው ሃብት ልማት ልዩ ትኩረት በመስጠት እንዲሁም የነፃ ንግድ ቀጠና ስምምነቶችን በማድረግ የቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ስበዋል፤ በዚሁ ባለፉት 30 ዓመታት 5-7 በመቶ ያልተቋረጠ እድገት በማስመዝገብ አስደናቂ የኢኮኖሚ እድገትን አረጋግጠዋል፡፡

ኢትዮጵያ በተመሳሳይ ሁኔታ በተለይም ከለውጡ ወዲህ በአንድ ክፍለ ኢኮኖሚ ላይ ከተንጠለጠለ የኢኮኖሚ ግንባታ ወደ ብዝሃ ሴክተር የኢኮኖሚ ግንባታ ተሸጋግራለች፡፡ በአገር በቀል የኢኮኖሚ እቅዷና ሪፎርሟ  ግብርናን፣ አምራች ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝም እና ለዲጂታል ኢኮኖሚ የኢኮኖሚ ግንባታዋ አዕማድ ወይም ምሳሶ በማድረግ ባለፉት 7 ተከታታይ ዓመታት ከሰባት በመቶ በላይ የኢኮኖሚ እድገት በማረጋገጥ ታሪካዊ ስራ አከናውናለች፡፡ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርቷንም በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ በእጥፍ አሳድጋለች፡፡

የቬየትናሞቹ ልምድና ተሞክሮም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ግንባታ አቅጣጫ ትክክለኛነትን በተጨባጭ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ከቬየትናም የተገኘው ልምድና ተሞክሮ ኢትዮጵያ የጀመረችውን ሪፎርም በማጠናከርና ሰላምና መረጋጋትን በመፍጠር በያዘችው መንገድ ከቀጠለች በአጭር ጊዜ ውስጥ ቬየትናም ካስመዘገበችው የኢኮኖሚ እድገት የላቀ እድገት ማስመዝገብ እንደምትችል የሚጠቁም ነው፡፡

ተሞክሮ ሁለት፣

70 በመቶ በላይ የሚሆኑ የቬየትናም ዜጎች 1990ዎቹ ዓመታት ከድህነት ወለል በታች ይኖሩ ነበር። ሆኖም ቬየትናም በተከተለችው የኢኮኖሚ ዕድገት አቅጣጫ በተለይም ለግብርና ልማት በሰጠቸው ልዩ ትኩረት 2020 ይህን አኃዝ ወደ 4% (በመቶ) ዝቅ እንዲል አድርጋለች:: የግብርና ሪፎርሟ ውጤታማ በመሆኑ ራሷን በምግብ ሰብል ከመቻል አልፋ በሩዝ፣ በፍራፍሬ፣ በቡና እና ሌሎች የግብርና ምርቶች በቀጣናው ከፍተኛ ላኪ ሀገር ሆናለች::

ይህ በጎ ልምድና ተሞክሮም፣ ኢትዮጵያ  ተረጅነትን በመቀነስ፣ ራስን በምግብ ሰብል በመቻል የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እያደረገችው ላለው ሁለንተናዊ ጥረት በእጅጉ ጠቃሚ አስረጂ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በግብርና ልማት በተለይም በስንዴ አብዮት ራስን ለመቻል ያደረገችው እንቅስቃሴ ስኬታማ ሆኗል፡፡ ከዚህ የተገኘውን ልምድ በመውሰድ አሁን ደግሞ መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ በሩዝ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ጀምራለች፡፡ በዚህም ረገድ የቬየትናሞች ስኬት ኢትዮጵያ በትክክለኛ አቅጣጫ እየተጓዘች መሆኗን ከማረጋገጥ ባለፈ ጠቃሚ ትምህርት የሚሰጥ ነው፡፡

በመሆኑም የጀመርናቸውን መልካም ስራዎች የሚያጠናክሩ የአገር ውስጥ ልምዶችን ከማጎልበት ባሻገር በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታዩ በጎ ልምዶች በመቀመር በግብርና ዘርፍ የተጀመረውን መነሳሳት ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ እንደ ቬየትናም ያሉ በግብርና ልማት ስራዎች ውጤታማ የሆኑ አገሮች ኢትዮጵያ ለምትካሂዳቸው የሪፎርም ስራዎች ጥሩ መነሻ ሆኖ የሚያገለግሉ ናቸው፡፡

ተሞክሮ ሶስት፣

ቬየትናም የዓለም ንግድ ድርጅትን ጨምሮ በቀጠናው ካሉ አህጉራዊ እና ቀጠናዊ ድርጅቶች ጋር በነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት ዙሪያ ሰፋፊ ድርድሮችን አካሂዳለች፡፡ በዚህም ረገድ ውጤታማ ሆናለች፡፡ በየዓመቱ 34 ቢሊየን ዶላር በላይ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መሳብ ችላለች፡፡ በተለይም እንደ ኤሌክትሮኒክስ፣ ጨርቃጨርቅና የጫማ አምራች ኢንዱስትሪዎችን መሳብ ችላለች፡፡ ይህም በቀጠናው ከፍተኛ የሚባል የኢንቨስትመን ስበት ማሳያ ነዉ፡፡

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የንግድ ድርጅት ጋር ብዙ ርቀት የተጓዘ ድርድሮችን በማካሄድ ላይ ትገኛለች፡፡ ድርድሮቹም ውጤት እየተገኘባቸው መጥቷል፡፡ በምስራቅ አፍሪካም ነፃ የንግድ ስምምነት ለመፍጠር ከሀገሮቹ ጋር በርካታ ድርጅሮችን እያካሄደች ነው፡፡ ይህም ውጤት እያስመዘገበ ነው፡፡

በአፍሪካ ህብረት የተቀመጠውን ግብ ለማሳካትም ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ስራ እያከናወነች ነው፡፡  ነፃ የንግድ ቀጠና ድርድር በማካሄድ ቬየትናምን ሰፊና ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እንድታገኝ ያስቻሏትን የድርድር መንገዶች፣ አሰራሮችና የህግ ማዕቀፎችን በመመርመር ኢትዮጵያ በተመሳሳይ ሁኔታ ለምትፈጽማቸው ስራዎች እንደየሁኔታው መጠቀም ይገባል፡፡

አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የቬየትናም የአምራች ኢንዱስትሪዎች ከፍተኛ ታሪፍ እየተጋረጠባቸው መጥቷል፡፡ በመሆኑም እንደ ኢትዮጵያ ዝቅተኛ ታሪፍ፣ ታዳሽ የሃይል አቅርቦት፣ ርካሽ ጉልበት፣ እየዘመነ የመጣ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ በአንድ ማዕከል ወይም አካባቢ የተሰበሰቡ ኢንዲስትሪዎች መጠናከር እና የነጻ የንግድ እና ኢኮኖሚ ዞኖች መፈጠር እንደ ቬየትናም ላሉ ሀገሮችና ባለሀብቶች ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታን ፈጥሮላቸዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትራችን ጉብኝት ከዚህ አኳያ ጥሩ ልምድ ለመቅሰም ብቻ ሳይሆን ባለሀብቶቹ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉም መንገድ የከፈተ ነው፡፡ ይህን ምቹ እድል አጠናክሮ መጠቀም ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡

ተሞክሮ አራት፣

ቬየትናሞች ለሰብአዊ ልማት በተለይም ደግሞ ለቴክኒክና ሙያ የሰጡት ልዩ ትኩረት ኢኮኖሚያቸው ይበልጥ እንዲያድግ ረድቷል:: የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ንጥር ቅባለቸው 99 በመቶ በላይ የደረሰ ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ንጥር ቅበላውም ወደ ዘጠና በመቶ የተጠጋ ነው፡፡ ይህ አሃዝ በመካከለኛ እድገት ደረጃ ካሉት ሀገሮች ከፍተኛው ነው፡፡ ቬየትናም በዓለም አቀፉ የሰብአዊ ልማት index መሰረት ከሲንጋፖር ቀጥላ ሁለተኛዋ የሰብአዊ ካፒታል የገነባች ሀገር ሆናለች፡፡

ኢትዮጵያም በቅርቡ ለመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ልዩ ትኩረት የሚሰጥ የትውልድ ግንባታ አቅጣጫን ተግባራዊ ማድረግ ጀምራለች፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ የቬየትናም ጉብኝትም ከዚህ አኳያ ጠቃሚ ልምድ የተገኘበት ነው፡፡ ቬየትናሞች የኢትዮጵያን ሰብዓዊ ሀብት ልማት ለማገዝ ቃል ገብተዋል፡፡ በየዓመቱ መጠነኛ ቁጥር ላላቸው የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ስኮላርሺፕ ለመስጠት እና በሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) አብሮ ለመስራት ፍላጎት   አሳይተዋል፡፡ ይህንኑም በአግባቡ መጠቀም ያስፈልገናል፡፡

በአጠቃላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) በቬየትናም የነበራቸው ቆይታ ስኬታማና የኢትዮጵያን አስፈላጊ አጋርነት ያረጋገጠ ነው። የልዑኩም ቆይታ የኢትዮጵያን ያለፉት 7 የለውጥ ዓመታት ተሞክሮ ለመቃኘትና የጉዞአችንን ትክክለኛነት ከማረጋገጥ ባለፈ መጪው ጊዜ አዲስ የታሪክ እጥፋት የምናስመዘግብበት እንዲሆን አቅም የፈጠረ ነው።

በቬየትናም የቆይታ ምዕራፍ ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትራችን የታደሙበትዘላቂ እና ሕዝብን ማዕከል ያደረገ አረንጓዴ ሽግግርበሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀው የቬየትናሙ የፒ4 ጉባኤ፣  ትርጉም ያለው ውጤት የሚያስገኙና ትልቅ አቅም ያላቸው ፕሮጀክቶች የታዩበት መሆኑ ታይቷል። የአረንጓዴ ልማት እድገትን ለማፋጠን፣ አዳዲስ አጋርነቶችን ለማጎልበት እና የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ለሚደረገው የጋራ ቁርጠኝነት ማሳያ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትራችን በመልዕክታቸው አስገንዝበዋል።

ጉባኤው 2027 ለሀገራችን ሌላ እድል አምጥቶና የመሪያችንንና ህዝባችንን ክብር ባረጋገጠ አኳሃን ኢትዮጵያ 5ኛውን የፒ4 ጉባኤ እንድታካሂድ ችቦ አረካክቧል። በመሆኑም ሀገራችን እንደ ቬየትናም በሌላ ምዕራፍ ልምድና ተሞክሮዋን፣ በብዝሃ እምርታና ስኬት ይዛ እንድትቀርብ ለማድረግ ርብርባችንን ከወዲሁ አጠናክረን ልንቀጥል ይገባል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም