ቀጥታ፡

በመዲናዋ ለበዓል የሚሆኑ የእርድ እንስሳት በበቂ መጠን ቀርበዋል - ሸማቾች

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 11/2017(ኢዜአ)፦ በመዲናዋ ለትንሳኤ በዓል የሚሆኑ የእርድ እንስሳት በበቂ መጠን መቅረባቸውን ኢዜአ ሲገበያዩ ያገኛቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለፁ።

ኢዜአ የትንሳዔ በዓልን ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ የእርድ እንስሳት የግብይት ሁኔታን ተዘዋውሮ ተመልክቷል።

በዚህም የቁም እንስሳት ግብይት አቅርቦት በተሻለ ሁኔታ መኖሩንና መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ መታየቱን ሸማቾች ተናግረዋል።

በሾላ ገበያ ዶሮ እና እንቁላል ሲገበያዩ ያገኘናቸው ወይዘሮ ሙሉ እመቤት ታደሰ፤ ለበዓሉ በቂ የእንስሳት አቅርቦት እንዳለ አስተያየታቸው ሰጥተዋል።

በቂ አቅርቦት መኖሩ ሁሉም ባለው አቅም መርጦ በመግዛት በዓሉን እንዲያከብር ያስችለዋል ሲሉ ነው የጠቀሱት።

በአዲሱ ገበያ ሲገበያዩ ያገኘናቸው አቶ ይታገሱ በቀለ እና ስዩም ተፈራ በበኩላቸው፤ የዘንድሮው የትንሳኤ በዓል መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ ቢኖረውም ገበያው ላይ በቂ አቅርቦት በመኖሩ እንደአቅማቸው መግዛታቸውን ገልጸዋል።

የበግና ፍየል ገበያ ከሌሎቹ የበዓል ጊዜያት ጋር ሲነጻጸር መጠነኛ ጭማሪ ቢያሳይም ከአርሶ አደሮቹ በጥሩ ዋጋ መግዛት መቻላቸውን አቶ ዘሪሁን ወልዴ የተባሉ ሸማች ተናግረዋል።

አቶ ምሳዬ ተፈራ፣ አቶ አንዷለም እሸቴ እና አቶ ዘለቀ እጅጋየሁ በሰንጋ ገበያው በቂ አቅርቦት መኖሩን ነው የተናገሩት።

አስተያየት ሰጪዎቹ በአሉን ስናከብር ጧሪ የሌላቸውንና አቅመ ደካማ ወገኖችን በመጠየቅና ካለን በማካፈል ሊሆን ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

የበዓሉ አስተምህሮም ይህንኑ የሚያጎለብት መሆኑን አመልክተው፤ የበዓሉን እሴት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም