ወላይታ ድቻ በአፍሪካ የቮሊቦል ክለቦች ሻምፒዮና የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደርጋል 

አዲስ አበባ ፤ሚያዚያ 12/2017 (ኢዜአ)፡-  ወላይታ ድቻ በ46ኛው የአፍሪካ የወንዶች የቮሊቦል ክለቦች ሻምፒዮና የመጀመሪያ ጨዋታውን ዛሬ ከሊቢያው ኢትሃድ ትሪፖሊ ጋር ያደርጋል። 

በሊቢያ ሚስራታ ከተማ የሚካሄደው ሻምፒዮና ትናንት ተጀምሯል።

በሻምፒዮናው ላይ 25 የአፍሪካ የቮሊቦል ክለቦች ተሳታፊ ሆነዋል። ክለቦቹ በአራት ምድብ ተከፍለው ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። 

ኢትዮጵያን ወክሎ በሻምፒዮናው የሚሳተፈው ወላይታ ድቻ በምድብ ሶስት ከሞሪሺየሱ ኦሊምፒክ ዲ ኪዩርፓይፕ አሶሴሽን፣ ከሩዋንዳው ኪርሄ ቮሊቦል ክለብ፣ ከኬንያው ፕሪዝንስ ኬንያ፣ ከካሜሮኑ ፓድ ቮሊቦል ክለብ እና ከሊቢያው ኢትሃድ ትሪፖሊ ጋር ተደልድሏል። 

ወላይታ ድቻ የመጀመሪያ ጨዋታውን ዛሬ ከቀኑ 10 ሰዓት ከሊቢያው ኢትሃድ ትሪፖሊ  ጋር ያደርጋል።

46ኛው የአፍሪካ የወንዶች የቮሊቦል ክለቦች ሻምፒዮና እስከ ሚያዚያ 22 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል። 

ሻምፒዮናው በአፍሪካ ቮሊቦል ኮንፌዴሬሽን አስተናጋጅነት ይሚካሄድ ነው።

እ.አ.አ በ1980 በተጀመረው የአፍሪካ የወንዶች የቮሊቦል ክለቦች ሻምፒዮና የግብጹ አል አህሊ 16 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዘዋል።

የቱኒዚያ ስፋክሲያን ስድስት ጊዜ አሸናፊ ሲሆን የግብጹ ዛማሌክ እና የቱኒዚያው ኤስፔራንስ ደ ቱኒዝ በተመሳሳይ አምስት ጊዜ ዋንጫውን ወስደዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም