የትንሳኤ በዓል ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ አገራት እየተከበረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የትንሳኤ በዓል ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ አገራት እየተከበረ ነው

አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 12/2017 (ኢዜአ) :- የትንሳኤ በአል በኢትዮጵያ በውብ አልባሳት በመድመቅ በባህላዊ ምግቦች ዝግጅት ታጀቦ፣ ጎረቤት ተጠራርቶና ዘመድ ተሰባስቦ የሚከበር ታላቅ ሃይማኖታዊ በዓል ነው።
ከእለተ ፋሲካ ቀደም ብሎ ፀሎተ ሃሙስ ከተከናወነ በኋላ እለተ አርብ ደግሞ ስቅለት በመሆኑ በስግደትና ፀሎት ይታሰባል፤ በእነዚህ ቀናት የበዓል ገበያ የእርድ እንስሳና የፍጆታ ምርቶችም ይሸመታሉ።
እለተ ፋሲካ እሁድ እለት በደማቅና በሚያምር ድባብ በየቤቱ በሚከናወን ድግስ ከረጅም ጊዜ ፆም በኋላ በርካቶች ስጋን ጨምሮ የእንስሳት ውጤቶችን በመመገብ በዓሉን በደስታ ያከብራሉ።
የፋሲካ በዓል ጥልቅ ሃይማኖታዊ ትንታኔ የሚሰጠውና በጥብቅ ዲስፕሊን የክርስቶስን ፍቅርና ለሰው ልጆች የዋለውን ውለታ በማሰብ የሚከናወን መሆኑም ይታወቃል።
ከኢትዮጵያም ውጭ በተለያዩ አገራት በልዩ ልዩ ዝግጅቶች የሚከበር ሲሆን የኒውዝላንድንና አውስትራሊያን ብናነሳ እለተ ፋሲካ በተለይም በመስቀል ቅርፅ የተሰሩ ጣፋጭ ዳቦዎችን በብዛት መመገብ የተለመደ መሆኑ ይነገራል።
በደቡብ ፓስፊክ ደግሞ በቤተ ክርስቲያን በመሰባሰብ የእምነቱ አባቶች እንዲሁም ምእመኑ ክርስቶስ ለሰው ልጆች የከፈለውን ዋጋ በማሰብ ያከብራሉ።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት የፋሲካ በዓል በተለያዩ ኃይማኖታዊ ሥርዓቶች የሚከበር መሆኑ ይታወቃል።
ኢትዮጵያዊያን በጎነትን በማሳየት፣ በመተሳሰብ፣ በመረዳዳትና በጋራ ተሰባስቦ በመብላትና በመጠጣት በታላቅ ድምቀት አክብረዋል።
በደቡብ አፍሪካ የፋሲካ በዓል የቤተሰብ መሰባሰቢያ ታላቅ የደስታና የአብሮነት ማሳያ በዓል እንደሆነ ይነገራል።
በናይጀሪያ እና ማዳጋስካር ደግሞ የመስቀሉን ሃይል የሚያሳዩ የመፅሃፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በማንሳትና በማብራራት ነው የሚያከብሩት።
የትንሳኤ በዓል በአህጉረ ኤዥያዋ ፊሊፒንስ ከማለዳው የምሮ ክርስቶስን በማሰብ በተለያዩ ዝግጅቶች የሚከበር መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በዚህ እለት ወንዶች የክርስቶስን ምስል ይዘው ወደ ቤተክርስቲያን ጉዞ በማድረግ እና ሴቶችም ተሰባስበው በተመሳሳይ ሁኔታ ጥቁር ልብስ በመልበስ ሞትን ድል አድርጎ መነሳቱን በማውሳት ወደ ቤተክርስቲያን በመጓዝ በጋራ ያከብሩታል።
በአውሮፓ አገራትም የፋሲካ በዓል አከባበር የካበተና የቆየ ታሪክ ያለው ሲሆን በተለይም በሮማኒያ፣ ሰርቢያ እና ግሪክ የጁሊያን ካላንደርን በመከተል በሌሎች ዓለማት ከተከበረ ከአንድ ወይም ሁለት ሳምንት በኋላ ነው የሚያከብሩት።
በጀርመንም የፋሲካ ዛፍ የሚሉትን በተለያዩ ቀለሞች ባሸበረቁ እንቁላሎች በማስዋብ የሚያከብሩ ይሆናል።
በፖላንድም እሁድ ማለዳ ላይ “ባባካ” እያሉ የሚጠሩትን ጣፋጭ ዳቦ በመመገብ በዓሉን ማክበር እንደሚጀምሩ ይነገራል።
በብራሰልስም በጎ ፈቃደኞች በሽዎች የሚቆጠሩ እንቁላሎችን በመጥበስና ኦምሌት በመስራት ትልቅ ማእድ አድርገው በጋራ በመመገብ ነው የሚያከብሩት።
በአሜሪካ እና በሌሎችም ዓለማት የፋሲካ በዓል ከመንፈሳዊ ስርአቱ በሻገር በየአገራቱ የተለያዩ ባህላዊ እሴቶችን በማከል የሚያከብሩት መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በዚህም መሰረት በዛሬው እለት ኢትዮጵያን ጨምሮ በተጠቀሱት አገራትና በሌሎችም በደማቅ ስነ ስርአት ተከብሯል።