በሠራተኞች ትጋት የካዛንችስ የኮሪደር ልማት የማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ ደርሷል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
በሠራተኞች ትጋት የካዛንችስ የኮሪደር ልማት የማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ ደርሷል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 12/2017 (ኢዜአ) :-በሠራተኞች ትጋት የካዛንችስ የኮሪደር ልማት የማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ ደርሷል ሲሉ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ በካዛንቺስ ለሚገኙ የኮሪደር ልማት ሰራተኞች ማዕድ አጋርተዋል።
ከንቲባዋ በእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸው፥ የኮሪደር ልማት ሰራተኞች ቀን ከሌሊት በመትጋት ከተማዋ ውብ ገጽታ እንድትላበስ ስላደረጉም ምስጋናቸውን ገልጸዋል።
በዓልን በሥራ ላይ ካላችሁ የኮሪደር ልማት ሰራተኞች ጋር ማሳለፍ የስራ ባህል ለመቀየር በሚደረገው ጥረት የራሱ የሆነ አወንታዊ ሚና አለው ሲሉም ነው የጠቀሱት።
በእናንተ ትጋት የካዛንቺስ የኮሪደር ልማት እየተጠናቀቀ ነው ያሉት ከንቲባዋ፥ የስራ ባህልንም የሚቀይር ውጤት እየተገኘ መሆኑን ተናግረዋል።
የኮሪደር ልማት የአዲስ አበባን ገጽታ ከመቀየር ባሻገር ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩንም አንስተዋል።
በአዲስ አበባ በኮሪደር ልማት የተመዘገበው ስኬት በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያን ገጽታ እየለወጠ መሆኑን ያነሱት ከንቲባ አዳነች፥ ለሥራ፣ ለመኖሪያና ለመዝናኛ ምቹ ከባቢ እንዲፈጠር ማድረጉንም ተናግረዋል።
በካዛንቺስ እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን ጠቁመው፥ ለዚህ ስኬት የሠራተኞች ትጋት ትልቅ ሚና ተጫውቷል፤ ከተማ አስተዳደሩ ለዚህም ምስጋናውን ያቀርባል ብለዋል።
በአዲስ አበባ ካዛንቺስ ለወራት በኮሪደር ልማት ሥራ የተሳተፈው ወጣት ሺፈራው ሌዳሞ ለኢዜአ በሰጠው አስተያየት በኮሪደር ልማት ስራ ላይ በመሳተፉ ደስተኛ መሆኑን ገልጿል።
በካዛንቺስ የሚገኘው የሴቶች አደባባይ ኮሪደር ልማት ላይ መሳተፉን የጠቀሰው ወጣቱ አደባባዩ እጅግ ተውቦ በማየቱ መደሰቱንም ተናግሯል።
ሌላው የኮሪደር ልማት ሰራተኛ ወጣት ወማ ቱንሲሶ በበኩሉ የኮሪደር ልማቱ ውጤታማ እንዲሆን የከንቲባ አዳነች ድጋፍና ክትትል ትልቅ ሚና መጫወቱን ጠቅሷል።
በዛሬው ዕለትም ከንቲባዋ በዓልን ከኛ ጋር በማሳለፋቸው ደስታ ተሰምቶኛል ሲሉም ሀሳቡን አካፍሏል።