የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ የትንሳኤ በዓልን ጤና ባለሙያዎች እና ታካሚዎች ጋር አከበሩ

አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 12/2017 (ኢዜአ):-የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከሚገኙ ጤና ባለሙያዎች እና ታካሚዎች ጋር የትንሳኤ በዓልን አክብረዋል። 

ዶክተር መቅደስ የጤና ባለሙያዎችን ያበረታቱ ሲሆን ለታካሚዎችም ስጦታ አበርክተዋል። 

ሚኒስትሯ የጤና ሙያ ራስን ሰጥቶ ህብረተሰቡን ማገልገል ዋንኛ መገለጫው ነው ብለዋል።

ለሕብረተሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት ከማሻሻል ጎን ለጎን የጤና ባለሙያውን ሕይወት ትርጉም ባለው መልኩ ለመቀየር ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በተመሳሳይ ዶክተር መቅደስ ዳባ ከሌሎች የሚኒስቴሩ አመራሮች ጋር በመሆን በሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ ተገኝተው ማዕድ በማጋራት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ሚኒስትሯ ለሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ 4 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ዘመናዊ የአልትራሳውንድ ማሽን ድጋፍ አበርክተዋል።

ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ ወላጅ አልባ ህጻናትን እና አረጋዊያንን ከወደቁበት አንስቶ ከመደገፍ ባሻገር ራሳቸዉን ችሎ ለሌሎችም እንዲተርፉ ከማድረግ አንጻር አርአያ በመሆን እያከናወነ ላለው ስራ ምስጋና አቅርበዋል። 

የሜሪጆይ ኢትዮጵያ መስራች እና ዋና ዳይሬክተር ሲሰተር ዘቢደር ዘዉዴ በበኩላቸው ሚኒስትሯ ላደረጉት የአልትራሳውንድ ማሽን ድጋፍ ምስጋና አቅርበው መሳሪያው ዘመኑ የደረሰበትን የምርመራ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ነው ብለዋል። 

ሜሪጆይ ኢትዮጵያ አራዳ ጊዮርጊስ በሚገኝ ማዕከሉ ከ4 ሺህ በላይ እንዲሁም በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ 67 ሺህ በላይ ወላጅ አልባ ህጻናትና አረጋዊያንን በመደገፍ አስፈላጊ እንክብካቤ እያደረገላቸው እንደሚገኝ መግለጻቸውንም የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም