ሊቨርፑል የሊጉን መሪነት ያጠናከረበት ወሳኝ ድል አስመዝግቧል - ኢዜአ አማርኛ
ሊቨርፑል የሊጉን መሪነት ያጠናከረበት ወሳኝ ድል አስመዝግቧል

አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 12 /2017 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ33ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ሊቨርፑል ሌይስተር ሲቲን 1 ለ 0 አሸንፏል።
ማምሻውን በኪንግ ፓወር ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ትሬንት አሌክሳንደር አርኖልድ በ76ኛው ደቂቃ የማሸነፊያዋን ጎል ከመረብ ጋር አገናኝቷል።
ውጤቱን ተከትሎ ሊቨርፑል ነጥቡን ወደ 79 ከፍ በማድረግ የሊጉን መሪነት አጠናክሯል።
ከተከታዩ አርሰናል ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት በድጋሚ ወደ 13 ከፍ አድርጓል።
ቀያዮቹ ዋንጫውን ለማንሳት የተቃረቡበትንም ወሳኝ ድል አስመዝግበዋል።
ሌይስተር ሲቲ በ18 ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ሽንፈቱን ተከትሎ ሌይስተር ሲቲ አምስት ጨዋታ እየቀረ ከሳውዝሃምፕተን ቀጥሎ ከሊጉ የወረደ ሁለተኛ ክለብ ሆኗል።