የአዳማ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በከተማዋ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የኑሮ ውድነትን በዘላቂነት ለማቃለል እየሰራ ነው - ከተማ አስተዳደሩ - ኢዜአ አማርኛ
የአዳማ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በከተማዋ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የኑሮ ውድነትን በዘላቂነት ለማቃለል እየሰራ ነው - ከተማ አስተዳደሩ

አዳማ፤ ሚያዝያ 13/2017(ኢዜአ)፦ የአዳማ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የግብርና እና የማምረቻ ኢንዱስትሪዎችን በውስጡ በማደራጀት በከተማዋ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥና የኑሮ ውድነትን በዘላቂነት የማቃለል ተግባራት እያከናወነ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ገለፀ።
የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሃይሉ ጀልዴ እንዳሉት አስተዳደሩ በከተማዋ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተለያዩ የከተማ ግብርና ኢንሼቲቮችን ቀርፆ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል።
በዚህም የአዳማ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የግብርና እና የማምረቻ ኢንዱስትሪዎችን በውስጡ በማደራጀት በከተማዋ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥና የኑሮ ውድነትን በዘላቂነት የማቃለል ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
የኢንቨስትመንት ግሩፑ በማህበር ተደራጅተው በወተት ልማት እና በዶሮ እርባታ ላይ የተሰማሩ ማህበራት ምርቶቻቸውን በስፋት ለገበያ እንዲያቀርቡ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የበዓል ገበያም የተረጋጋ እንዲሆን ሁኔታዎችን በማመቻቸትና የግብይት ቦታን በማዘጋጀት ጭምር በኢንቨስትመንት ግሩፑ ውስጥ የተደራጁ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለተጠቃሚው የማድረስ ተግባር ተከናውኗል ብለዋል።
አስተዳድሩ ከ2ሺህ 900 በላይ የወተት ላሞች፣ የዶሮ እርባታና የእንቅላል ምርት ማዕከላት እንዲሁም የምግብ ዘይት ማምረቻ ኢንዱስትሪን በራሱ በማቋቋም የዋጋ ንረት ተፅዕኖን በዘላቂነት የመከላከል ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ለበዓላቱም ከሳምንታት በፊት ዝግጅት በማድረግ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች በስፋት ወደ ግብይት ማዕከላት እንዲገቡ በማድረግ የዋጋ ንረትን የመቆጣጠር ስራ ተሰርቷል ብለዋል።
በተለይም ለዘንድሮው የፋሲካ በዓል መስተዳድሩ የእንስሳትና ተዋፅኦ ምርቶችን ማለትም 10ሺህ ዶሮና ከ100ሺህ በላይ የእንቁላል ምርት፣ ወተትና የወተት ተዋፅኦ እንዲሁም አትክልትና ፍራፍሬን ለገበያ እንዲቀርቡ ማድረጉን ገልፀዋል።
የአዳማ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የኑሮ ውድነትን በዘላቂነት ለመግታት በወተት ላሞች ልማት፣ በዶሮ እርባታና በእንቁላል ምርት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት እንዲሁም በእንስሳትና ዶሮ መኖ ማቀነባበር ስራ ላይ በመሰማራት ከውጭ የሚገባውን መኖ መተካት የሚያስችል ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ ከከተማ አስተዳደሩ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።