የኢትዮጵያ የባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን እና ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን እና ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 13/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን እና ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን የኢትዮጵያ የባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ህይወት መሀመድ እና የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ፈቀደ ቱሊ(ዶ/ር) ፈርመውታል።
ስምምነቱ በባህል ስፖርቶች ጥናትና ምርምር፣ ትምህርትና የባለሙያዎች አቅም ግንባታ ላይ በጋራ መስራት የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ የባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ህይወት መሀመድ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት፤ የሁለትዮሽ ስምምነቱ በሀገር ውስጥ የሚገኙ በርካታ የባህል ስፖርቶችን ለማጥናት እና ለማሳደግ ብሎም በህብረተሰቡ ዘንድ ተዘውታሪ ለማድረግ ነው።
እንዲሁም ባህላዊ ስፖርቶችን በማጥናት በአለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ እና ለማስፋፋት ያለመ መሆኑንም ገልፀዋል።
የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ፈቀደ ቱሊ(ዶ/ር) በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ዘርፎች በእውቀት እና ክህሎት ብቁ መምህራንና የትምህርት አመራሮችን እያፈራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የሀገሪቱን ባህላዊ ስፖርቶችን ለማሳደግ ስምምነቱ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ ዩኒቨርሲቲው የሚጠበቅበትን እንደሚያደርግ አመልክተዋል።