በአስተዳደሩ የሴፍቲኔት ፕሮግራም ተጠቃሚዎችን የኑሮ ደረጀ የሚያሻሽሉ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው

ሰቆጣ፤ ሚያዚያ 13/2017(ኢዜአ)፦ በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር የሴፍቲኔት ፕሮግራም ተጠቀሚዎችን ከተረጂነት ማውጣት የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን የአስተዳደሩ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፅህፈት ቤት አስታወቀ።

የፅህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ምህረት መላኩ ለኢዜአ እንደገለፁት አካባቢው ዝናብ አጠር በመሆኑ ህብረተሰቡ በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት በሴፍቲኔት ፕሮግራም ያማገዝ ሥራ እየተሰራ ነው።

በአስተዳደሩ ከሴፍቲኔት ፕሮግራም ተጠቃሚዎች ውስጥ በአሁኑ ዙር 55ሺህ 362 የሚሆኑትን ከተረጂነት ለማላቀቅ ታቅዶ እየሰራ ነው።

ዘንድሮም በዘላቂ የኑሮ ማሻሻያ መርሃ ግብር 217 ሚሊዮን 470ሺህ ብር በመመደብ 12ሺህ 300 የሴፍቲኔት ተጠቃሚዎችን በተለያዩ የልማት ዘርፎች የማሰማራት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ ውስጥም በአስተዳደሩ ለሚገኙ 400 እማወራና አባወራዎችን በመስኖ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ በ16 ሚሊዮን ብር የውሃ መሳቢያ ጀነሬተር በመግዛት ማሰራጨቱን ተናግረዋል።

በተጨማሪም 1ሺህ 204 የሴፍቲኔት ተጠቃሚዎች በመረጡት የስራ ዘርፍ ቢዝነስ ፕላን በማዘጋጀት ለእያንዳንዳቸው 33 ሺህ ብር እንደተሰጣቸው አስረድተዋል።

ድጋፍ የተደረገላቸው ተጠቃሚዎችም በአትክልትና ፍራፍሬ ልማትና ሌሎች የስራ ዘርፎች ፈጥነው ወደ ስራ በመግባት ኑሯቸውን በዘላቂነት እንዲቀይሩ በየደረጃው ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል።

ከአስተዳደሩ ነዋሪዎች መካከል አቶ ሞገስ ቸኮለ እንዳሉት በተደረገላቸው የውሃ መሳቢያ ሞተር አንድ ሄክታር መሬት የሚደርስ መሬታቸውን በመስኖ ማልማት መጀመራቸውን ተናግረዋል።

አሁን ላይ በተደረገላቸው ድጋፍ በምግብ ራሳቸውን በመቻል ኑሯቸውን ለማሳደግ ተግተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ሌላዋ ነዋሪ ወይዘሮ ኪሮሱ ወናይ በበኩላቸው በተደረገላቸው የውሃ መሳቢያ ሞተር ከልጆቻቸው ጋር በመስኖ ልማቱ ተጠቃሚ ለመሆን ጠንክረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በብሄረሰብ አስተዳደሩ በአጠቃላይ 151ሺህ 869 የህብረተሰብ ክፍሎች የሴፍቲኔት ተጠቃሚ እንደሆኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም