ቬይትናም ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ ለመገንባት የምትከተለው የተሰናሰለ የሰው ሃብት ልማት ትምህርት የሚወሰድበት ነው - ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 13/2017(ኢዜአ)፦ ቬይትናም ተወዳዳሪ የኢኮኖሚ ሥርዓት ለመገንባት የምትከተለው የተሰናሰለ የሰው ሃብት ልማት ትምህርት የሚወሰድበት መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው የተመራ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ልዑክ በቬይትናም ይፋዊ የስራ ጉብኝት አድርጎ ተመልሷል።

የልዑኩ አባል የነበሩት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል የቬይትናም ይፋዊ የስራ ጉብኝትን አስምልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም የቬይትናም የስራ ጉብኝት የኢትዮጵያን የልማት አቅጣጫ ከሌላው ዓለም ጋር በማገናዘብ ያልታዩና ትምህርት የሚወሰድባቸውን ተሞክሮዎች ለመቅሰም ዕድል የሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

ቬይትናም እንደኢትዮጵያ ሁሉ አስቸጋሪ ጉዳዮችን በማለፍ በብዝኅ የኢኮኖሚ የልማት አቅጣጫ ቅኝት ዕድገትን በማስቀጠል ምቹ ዕድል የፈጠረች ሀገር መሆኗን አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ ካለፉት ሰባት ዓመታት ጀምሮ ለብዝኅ የኢኮኖሚ ልማት አቅጣጫ ትኩረት መሰጠቱ ሁለንተናዊ የዕድገትና ብልጽግና ዕድሎችን ፈጥኖ ለመጠቀም ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አስረድተዋል።

ቬይትናም ከግብርና መር ኢኮኖሚ በመላቀቅ ስኬት እያስመዘገበች የምትገኝበት የከተማና ገጠር ልማት ተግባርም በኢትዮጵያ ተስፋ ሰጪ ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የእኛ አቅጣጫ ነባራዊ ሁኔታን በመጠቀም ዕድገትን የሚያመጣ ነው ያሉት ሚኒስትሯ÷ በቬይትናም ቆይታም የተያዘው አቅጣጫ በትክክለኛ መንገድ መሆኑ ግንዛቤ የተወሰደበት ነው ብለዋል።

ቬይትናም በሰው ሃብት ልማት የትምህርትና ስልጠና ያደረገችው ቁልፍ ሽግግርም ለተከተለችው የልማት አቅጣጫ ምላሽ መስጠት በሚያስችል መልኩ የተቃኘ ሥርዓት መሆኑን አንስተዋል።

የቬይትናም መደበኛና ኢ-መደበኛ የትምህርትና ስልጠና የሰው ሃብት ልማት በአነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ ለመገንባት የተሰጠው ተልዕኮ ልምድ የሚወሰድበት ነው ብለዋል።

በዚህ መነሻነትም በጉብኝቱ ወቅት በኢትዮ-ቬይትናም መካከል የሰው ሃብት ልማት ምርታማነትን የሚያሳድግ የትምህርትና ስልጠና የትብብር መግባቢያ ስምምነት መደረጉን አስረድተዋል።

በኢትዮጵያም በአነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት ፈጠራን የሚያበረታታ ገበያ መር የሰው ሃብት ልማት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያም በራሷ እሳቤና አቅጣጫ ሁለንተናዊ ብልጽግናን እውን ለማድረግ ስኬት እያስመዘገበች የምትገኝ ሀገር መሆኗን አብራርተዋል።

በቬይትናም ጉብኝትም የእርስ በእርስ ልምድና ተሞክሮን በመጋራት የሀገራቱን ዕድገት ለማስቀጠል ትምህርት የተወሰደበት መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም