ፖሊስ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያዎችን ከ146 ተጠርጣሪዎች ጋር መያዙን ገለጸ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 13/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በ2017 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት በርካታ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያዎችን ከ146 ተጠርጣሪዎች ጋር መያዙን አስታውቋል፡፡

ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርን ለመከላከል በተደረገ ኦፕሬሽን፤ 121 የጦር መሣሪያዎችን ከመኖሪያ ቤቶች፣ 8 ሺህ 989 ከፀረ-ሰላም ኃይሎች እና 36 የጦር መሣሪያዎችን በኬላዎች ላይ መያዙን ገልጿል፡፡

በተጨማሪም 6 ሺህ 351 የተለያዩ የጦር መሣሪያ ጥይቶች ከመኖሪያ ቤቶች፣ 8 ሺህ 989 ከፀረ-ሰላም ኃይሎች፣ 51 ሺህ 846 በኬላዎች እንደተያዙ የፌዴራል ፖሊስ መረጃ ያሳያል።

እንዲሁም 236 የተለያዩ የጦር መሣሪያ ካዝናዎች በመኖሪያ ቤቶች እና 148 በኬላዎች ላይ መያዛቸው ተጠቁሟል፡፡

በተመሳሳይ 1 ብሬን ከፀረ-ሰላም ኃይሎች፣ 2 ብሬን በኬላዎች የተያዘ ሲሆን፤ 31 የተለያዩ ቦምቦች ከመኖሪያ ቤቶች፣ 25 ቦምቦችን ከፀረ-ሰላም ኃይሎች፣ 122 ቦምቦችን በኬላዎች መያዙን ፖሊስ አስታውቋል፡፡

32 የተለያዩ ሕገ-ወጥ ሽጉጦች ከመኖሪያ ቤቶች፣128 ሽጉጦች ከፀረ-ሰላም ኃይሎች፣ 102 በኬላዎች መያዝ መቻሉንም ፖሊስ ጠቅሷል።

1 ስናይፐር ከመኖሪያ ቤቶች እንዲሁም 1 ስናይፐር ከፀረ-ሰላም ኃይሎች በኤግዚቢትነት መያዙን እና 146 ተጠርጣሪዎችም በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አስረድቷል፡፡

ሕብረተሰቡ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርን ሲመለከት በዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ (EFPApp) እና በ991 ነፃ የስልክ መስመር ጥቆማ በመስጠት የዜግነት ድርሻውን እንዲወጣ ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም