የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቬይትናም ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት የትብብር አድማስ ያሰፋ ነው - ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 13/2017(ኢዜአ)፦ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የቬይትናም ጉብኝት ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን የትብብር አድማስ ያሰፋ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር) ገለፁ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የቬይትናም ይፋዊ ጉብኝትን አስመልክቶ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር) ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር) እንዳሉት ቬይትናም በሩዝ፣ በቡናና በሌሎች የግብርና ምርቶች ራሷን ከመቻል አልፋ ከፍተኛ ምርት ወደ ውጭ የምትልክ ሀገር ናት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከሀገሪቱ መሪዎች ጋር ባደረጓቸው ውይይቶች ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በምታደርገው ጥረት ከስንዴ ቀጥሎ ለሩዝ ምርት ትኩረት መስጠቷ መገለፁን አውስተዋል።

ቬይትናም የሩዝ ምርትን ለማስፋፋት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በቡና ምርት እና በምግብ ሰብል ራስን ለመቻል በሚደረገው ጥረት ከፍተኛ ልምድ ማግኘት የሚቻልባት ናት ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ የደን ሽፋንን ለማሳደግና የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት ከቬይትናም ጋር ተመሳሳይና ልምድ የሚገኝበት እንደሆነም ነው ያስረዱት።

ቬይትናም ከፍተኛ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በመሳብ ኤክስፖርት መር ኢኮኖሚ መገንባቷን ጠቅሰው፥ ለትምህርት ከፍተኛ ትኩረት መስጠቷ ጠቅሟታል ብለዋል።

በአምራች ኢንዱስትሪ በከፍተኛ ቴክኖሎጂ የታገዘ ኢንዱስትሪ መገንባቷን በማውሳት፥ ኤሌክትሮኒክስ፣ ጨርቃጨርቅና የጫማ ምርት በስፋት እያመረተች ወደ ውጭ እንደምትልክም አስረድተዋል።

ኢትዮጵያም ተኪ ምርቶችን ለማምረት በተለይ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በጨርቃጨርቅና በግብርና ምርቶች ማቀነባበር ላይ እየሰራች በመሆኗ ከቬይትናም ልምድ መቅሰም የሚቻልበት ሁኔታ እንዳለ ገልፀዋል።

በሃዋሳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን የቬይትናም ባለሃብቶች ገብተው እየሰሩ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ የሀገሪቱ ባለሀብቶች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በነበራቸው ውይይት በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው መግለጻቸውንም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩና ልዑካቸው በከተማ ግንባታ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን መጎብኘታቸውንና በዚህም የኮሪደር ልማትን ይበልጥ ማጎልበት የሚያስችሉ ልምዶች የተቀሰሙበት ነው ብለዋል።

በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በጋራ ልማት በተለይም በድህነት ቅነሳ ላይ ከቬይትናም ጋር መስራት የሚያስችሉ ውይይቶች በማድረግ መግባባት መፈጠሩን ጠቁመዋል።

የቬይትናም መሪዎች ኢትዮጵያ ቬይትናምን ከአፍሪካ ጋር የምታስተሳስር ስትራቴጂካዊ አጋር አድርገው እንደሚወስዷት መግለጻቸውንም አንስተዋል።

ኢትዮጵያም በእስያ ለምታደርጋቸው ግንኙነቶች ቬይትናምን ስትራቴጂካዊ አጋር አድርጋ መውሰድ እንደምትችል መገንዘብ መቻሉንም ነው ያብራሩት።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቅርቡ ወደ ሀኖይ ቀጥታ በረራ ለመጀመር ስምምነት ማድረጉ ኢትዮጵያን እና አፍሪካን ከቬይትናም ጋር ለማገናኘት ድልድይ ሆኖ እንደሚያገለግል ገልፀዋል።

የቱሪዝም፣ የማኑፋክቸሪንግና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን እንደሚያጠናክርም ጨምረው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ልዑክ በቬይትናም ባደረገው ውይይት ሁለቱ ሀገራት በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በትምህርትና ሌሎች ዘርፎችም የትብብር አድማሳቸውን ለማስፋት መስማማታቸውን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም