በኦሮሚያ ክልል የመኖሪያ ቤቶችን ችግር በዘላቂነት መፍታት የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው - የክልሉ ከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ

ሚያዚያ 13/2017(ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት ከግሉ ዘርፍ ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑን የክልሉ ከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ አስታወቀ።

የኦሮሚያ ከተማና ቤቶች ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ብርሃኑ በቀለ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በክልሉ በተለይም በከተሞች ያለው የመኖሪያ ቤት ፍላጎትና አቅርቦት አይመጣጠንም።

ችግሩን ለመቅረፍ የክልሉ መንግስት የተለያዩ መርሃ ግብሮችን ቀርጾ እየሰራ መሆኑን አቶ ብርሃኑ በቀለ ተናግረዋል።

ከእነዚህም መካከል መንግስት በራሱ አቅም የሚያከናውናቸው ተግባራት፣ በግሉ ሴክተር ተሳትፎ፣ በማህበራትና በበጎ ፈቃደኞች መኖሪያ ቤቶች እየተገነቡ ነው ብለዋል።

በዚህም በክልሉ የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመቃለል በ2017 በጀት ዓመት ከ129ሺህ 900 በላይ ቤቶች ተገንብተዋል ብለዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን  ከቤት ኪራይ ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ለመፍታትም ብዙ ስራ መሳራቱን ገልጸዋል።

በተለይም ቢሮው የአከራይና ተከራይ መብት ሚዛናዊ በሆነ መልክ ለማስተዳደርና ዘርፉን በሕግ ለመምራት በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የወጣውን አዋጅ መሰረት በማድረግ በክልሉ አስፈላጊ መመሪያዎችን በማዘጋጀት ተግባራዊ እያደረገ ነው ብለዋል።

በዚህም መሰረት ከተከራይና አከራይ ስምምነት ውጪ አከራይ ተከራይን እስከ ሁለት ዓመት ድረስ ከተከራየው ቤት ማስወጣትም ሆነ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ እንዳይችል መደረጉን ገልጸዋል።

በመመሪያው መሰረት እስከሁን ከ117ሺህ 900 በላይ የመንግስት ቤቶች እና 148ሺህ በላይ የግል የኪራይ ቤቶች ውል በአሰራሩ ተመዝግቧል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም