3ሺህ 285 ኢትዮጵያውያን ከሳዑዲ አረቢያ ወደ ሀገራቸው ተመለሱ

 

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 13/2017(ኢዜአ):- በሳዑዲ ዓረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ 3ሺህ 285 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሳምንቱ ውስጥ በተደረገ የዘጠኝ ዙር በረራ የተመለሱት 2ሺህ 747 ወንዶች፣ 508 ሴቶች እና 30 ጨቅላ ህፃናት ሲሆኑ ከተመላሾች መካከል 159 እድሜያቸው ከአስራ ስምንት አመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ይገኙበታል።

በአራተኛው ዙር በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን 50ሺህ ዜጎችን የመመለስ ስራ መጋቢት 3 ቀን 2017 ዓ.ም መጀመሩ ይታወቃል።

በዚህም እስከ አሁን 18ሺህ 969 ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገር መመለስ መቻሉ ተገልጿል።

ሚኒስቴሩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻና አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት ለተመላሽ ዜጎች በአየር ማረፊያና በማቆያ ማዕከላት ተገቢውን ድጋፍ እና እንክብካቤ የማድረግ እና ከቤተሰብ ጋር የማቀላቀል ስራም እየሰራ እንደሚገኝ በመረጃው አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም