በክልሉ ለመኸር እርሻ ከ100 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሮች እየተከፋፈለ ነው

መቀሌ፤ ሚያዚያ 13/2017(ኢዜአ)፦ በትግራይ ክልል ለመኸር እርሻ ከ100 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሮች እየተከፋፈለ መሆኑን በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ በ2017/18 የምርት ዘመን የኩታ ገጠም አስተራረስ እና የእርሻ ሜካናይዜሽንን የማጎልበት ተግባር ትኩረት እንደተሰጠው ተገልጿል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አበራ ከደነው፤ በተያዘው የመኸር ወቅት ለአርሶ አደሩ የሚያስፈልገውን የምርጥ ዘር እና ሌሎች የግብአት አቅርቦት ሟሟላት የሚያስችሉ ተግባራት ቀደም ብለው መጀመራቸውን ገልጸዋል።

በዚህም መሰረት ባለፈው የምርት ዘመን በአርሶ አደሩ እና በምርምር ተቋማት ከተባዙት የተለያዩ የሰብል ዓይነቶች ምርጥ ዘር የመሰብሰብ እቅድ ተይዞ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

ከኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን እና ከህብረት ስራ ማህበራት ዩኒየኖች ጋር በመተባበር ለምርት ዘመኑ የሚሆን ከ100ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለማቅረብ ታቅዶ አሁን በስርጭት ላይ ይገኛል ብለዋል።


 

በክልሉ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ በኩታ ገጠም/ክላስተር/ እርሻ የስንዴ፣ የማሽላ፣ የጤፍና የሰሊጥ እና ሌሎች ምርቶችን ለማልማት 250ሺህ ሄክታር መሬት መዘጋጀቱንም ተናግረዋል።

ከ130ሺህ ሄክታር የሚበልጠውን መሬትም በትራክተሮች በሜካናይዜሽን ማልማት የሚያስችል የተሟላ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

በጊዜያዊ አስተዳደሩ የክልሉ እርሻ ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ተክላይ አበበ(ዶ/ር)፤ የምርጥ ዘር አቅርቦትን ለማሳለጥ በ947 ሄክታር መሬት ላይ የምርጥ ዘር ብዜት ስራ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

በዚህም መሰረት በመጪው ክረምት ከ800 በላይ ኩንታል የመስራችና ቅድመ መስራች ምርጥ ዘር ለማከፋፈል መታቀዱን ገልፀዋል።

በአክሱም ከተማ የሚገኘው የምዕባለ የምርጥ ዘር ማባዛትና ግብይት ዩኒየን ስራ አስኪያጅ አቶ ግሩም ገብረሰላማ በበኩላቸው ዩኒየኑ ግብርናን ለማዘመንና ምርትን በጥራትና በመጠን ለማሳደግ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

ዩኒየኑ ከምርምር ማዕከላት የሚወጣን ምርጥ ዘር የማባዛትና የማከፋፈል ስራ በማከናወን የግብርና ግብዓቶችን ለሟሟላት ጥረት እያደረገ መሆኑና ለመኸር ወቅትም 7ሺህ 400 ኩንታል ምርጥ ዘር ለማከፋፈል ማቀዱን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም