በወልቂጤ ከተማ 25 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የኮሪደር ልማት ሥራ እየተፋጠነ ነው - አስተዳደሩ

ወልቂጤ፤ ሚያዚያ 13/2017(ኢዜአ)፦ በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ 25 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የኮሪደር ልማት ግንባታ ሥራ እየተፋጠነ እንደሚገኝ የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።

ነዋሪዎች በበኩላቸው በከተማዋ የኮሪደር ልማት ሥራው እንዲጠናከር ልማቱ በሚከናወንበት አካባቢ ንብረታቸውን በማንሳትና ይዞታቸውን በመልቀቅ የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን አስታውቀዋል።


 

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ሙራድ ከድር ለኢዜአ እንደገለጹት በከተማዋ 25 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የኮሪደር ልማት ሥራ በመፋጠን ላይ ይገኛል።

የኮሪደር ልማቱም በወልቂጤ ከተማ የሚካሄደውን ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ በሚያሳልጥና የነዋሪውን የልማት ፍላጎት በሚያሳካ መልኩ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኮሪደር ልማቱ 25 ኪሎ ሜትር እንደሚያካትት ገልጸው፣ ልማቱን ውጤታማ ለማድረግም ህዝብን በማወያየት በማሳተፍና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ልምድ መወሰዱን ገልጸዋል።

እንደ ከንቲባው ገለጻ የኮሪደር ልማት ሥራው በከተማው በአራት ሳይቶች ተለይቶ እየተከናወነ ይገኛል።

እነዚህም በተለምዶ አደባባይ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ አንስቶ እስከ ኮሌጅ፣  ከአፓርታማ እስከ ጉብሬ አደባባይ፣ ከጉብሬ አደባባይ ታች ገበያ ወይም መስጊድ እና ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ እስከ ጉብሬ አደባባይ ድረስ ያካተተ ነው።


 

የኮሪደር ልማት ሥራው የአረንጓዴና የመዝናኛ ስፍራዎች፣ የእግረኛ መንገዶች፣ የሳይክል መጋለቢያ እንዲሁም መናፈሻዎችን ባካተተ መልኩ ነው እየተከናወነ መሆኑን ከንቲባው ጠቁመዋል።

በልማቱ ከተማዋን ከማስዋብና ተወዳዳሪነቷን ከማሳደግ ባለፈ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ጠቅሰው፣ የህብረተሰቡም የሥራ ባህል እየተቀየረ መምጣቱን ነው የተናገሩት።

በግንባታ ሂደት ላይ ለሚገኘው የኮሪደር ልማት ሥራ 400 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ከአስተዳደሩ እና ከማህበረሰቡ ተሳትፎ  መመደቡንም  አክለዋል።


 

በኮሪደር ልማት ሥራው በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የጉልበት ሥራ በማገዝ ልማቱ እንዲፋጠን የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን ወጣት ቶፊቅ ኢንድሪያስ ተናግሯል።

በተለያዩ ከተሞች የተተገበረው የኮሪደር ልማት ሥራ ያስገኘውን ጥቅም በማየቱ ለድጋፍ መናሳቱን ጠቁሞ፣ የከተማው ወጣቶችም ልማትን ከመጠየቅ ባለፈ ለልማቱ ውጤታማነት የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለባቸው መክሯል።


 

ለከተማዋ ልማት የበኩላቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን የተናገሩት ደግሞ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ አብዱልሰመድ አስፋው፣ በአሁኑ ወቅት የተጀመሩ የኮርደር ልማት ሥራዎች ከተማዋ ለረጅም ዓመታት ሳታድግ የቆየችበትን ሁኔታ የሚቀይር መሆኑን  አስረድተዋል።

በተለይም ከከተማዋ መንገድ መጥበብ ጋር ተያይዞ በዋና መንገድ የሚስተዋለውን የትራፊክ እንቅስቀሴ መጨናነቅ በኮሪደር ልማቱ መፍትሄ ይሰጣል የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም