በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ከተለያዩ አካላት ሀብት በመሰብሰብ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻልና የመምህራንን አቅም መገንባት ተችሏል - ትምህርት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 13/2017(ኢዜአ)፦ በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ከተለያዩ አካላት ሀብት በመሰብሰብ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻልና የመምህራንን አቅም መገንባት እንደተቻለ የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል ሀገር የሚገነባ ትውልድ መፍጠር የሚያስችለውን ሀገር አቀፍ የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ በሰኔ ወር 2015 ዓ.ም በይፋ ማስጀመራቸው ይታወቃል፡፡

በዚህም በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ከራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል በተጀመረው ንቅናቄ ተስፋ ሰጪ ውጤት ተገኝቷል፡፡

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ በቂ እውቀትና ክህሎት ያላቸው ተማሪዎችን ማፍራት የሚያስችል የተሳለጠ የመማር ማስተማር ሥርዓት ተፈጥሯል።

በእውቀትና በክህሎት የዳበረ ትውልድ ለመፍጠር በአጠቃላይ የትምህርት ስርአቱ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ በመገንዘብ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡

የትምህርት ፍኖተ ካርታ፣ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ፣ እንዲሁም የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ግባቸው ብቁና አምራች ዜጋ መፍጠር የሚያስችል የተሳለጠ የመማር ማስተማር ሥርዓት መፍጠር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ከተጀመረ ጀምሮ እስካሁን ከ82 ቢሊዮን ብር በላይ ከተለያዩ አካላት ሀብት በመሰብሰብ የትምህርት ጥራትን የሚያረጋግጡ ሥራዎችን መሥራት ተችሏል ብለዋል፡፡

ንቅናቄው በሺዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል፣ አዳዲስ ትምህርት ቤቶችን መገንባት እንዲሁም በቂ የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችን ማቅረብ ያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም ተማሪዎች ጊዜያቸውን በትምህርት ቤቶች ማሳለፍ እንዲችሉ የተሟላ ቤተ ሙከራ፣ ቤተ መጽሐፍት፣ ወንበሮችና ሌሎች ግብዓቶች እንዲሟሉ ተደርጓል ብለዋል፡፡

ንቅናቄው ትምህርት ብዙ ሀብት የሚጠይቅ መሆኑንና ከመንግሥት ባሻገር የግሉ ዘርፍ በንቃት መሳተፍ እንዳለበት ለማህበረሰቡ ግንዛቤ መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡

የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የመምህራንን አቅም መገንባት ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ የመምህራንን ብቃትና ተነሳሽነት ለማሳደግ የመምህራንና ትምህርት ቤቶች አመራር ሥልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡

መምህራን በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ላይ በቂ መረዳትና እውቀት ኖሯቸው ተማሪዎችን ማብቃት የሚችሉበት እድል መፈጠሩን አረጋግጠናል ብለዋል፡፡

በሀገር አቀፍ የተማሪዎች ምገባ ስርዓት ተማሪዎች ትምህርታቸውን በንቃት የሚከታተሉበት እድል ተፈጥሯል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ምገባው ለወላጆች እፎይታን በመስጠትና የሥራ ዕድል በመፍጠር መልከ ብዙ ጥቅሞች ማስገኘቱን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም