በኢትዮጵያ የባህል ስፖርቶችን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው - ፌዴሬሽኑ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 13/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን በኢትዮጵያ የባህል ስፖርቶችን ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትኩረት እየሰራ መሆኑን የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ህይወት መሐመድ ገለፁ።

የኢትዮጵያ የባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽንና ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ዛሬ ተፈራርመዋል።


 

ስምምነቱን የኢትዮጵያ የባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ህይወት መሐመድ እና የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ፈቀደ ቱሊ(ዶ/ር) ፈርመውታል።

ስምምነቱ በባህልና ስፖርቶች ጥናትና ምርምር ለማከናወን እንዲሁም፣ በባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና ላይ በጋራ መስራት የሚያስችል መሆኑ ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ የባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ህይወት መሐመድ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት፤ ፌዴሬሽኑ የባህል ስፖርትን ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት ጋር አየሰራ ነው።

ከኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ጋር የተደረሰው የሁለትዮሽ ስምምነት በርካታ የባህል ስፖርቶችን ለማጥናት እና ለማሳደግ ብሎም በህብረተሰቡ ዘንድ ተዘውታሪ ማድረግ የሚያስችል ነው ብለዋል።


 

የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ፈቀደ ቱሊ(ዶ/ር) በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ዘርፎች በእውቀት እና ክህሎት ብቁ መምህራን እና የትምህርት አመራሮችን እያፈራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ስምምነቱ የሀገሪቱን የባህል ስፖርቶች ለማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ ዩኒቨርሲቲው የሚጠበቅበትን ሃለፊነት በአግባቡ እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም