ኢትዮጵያ በግብርና ልማት ለሌሎች ሀገራት ተምሳሌት የሚሆኑ ሥራዎችን እያከናወነች ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 13/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጰያ በግብርና ልማት ለሌሎች ሀገራት ተምሳሌት የሚሆኑ ሥራዎችን እያከናወነች መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎችን አፈጻጸም በተመለከተ ባለድርሻ አካላት ግምገማ አድርገዋል።

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) አባል ሀገራት የግብርና ልማት አፈጻጸምን በተመለከተ የአፍሪካ የግብርና ልማት ፕሮግራም በየሁለት ዓመቱ ይገመግማል።

ሀገራቱ ለፕሮግራሙ ሪፖርት ከማድረጋቸው በፊት ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የውይይት መድረክ በማዘጋጀት የየሀገራቸውን አፈጻጸም ይገመግማሉ።

በዚህ መሰረት ኢትዮጵያም የግብርና ልማት ስራዎቿን አፈጻጸም ገምግማለች።

በግብርና ሚኒስቴር የሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ዜና ሃብተወልድ እንደሚሉት፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ የግብርና ልማት ፕሮግራም የተሻለ አፈፃፀም አላት።

ፕሮግራሙ ያስቀመጣቸው መስፈርቶችን በልማት ዕቅዷ በማካተት ተግባራዊ ማድረጓ ለውጤቱ መገኘት ትልቅ ድርሻ ማበርከቱን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በስንዴ ልማት፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በሌማት ትሩፋትና በሌሎች የግብርና ልማት ስራዎች እያስመዘገበችው ያለው ስኬት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ የሚሆን ነው ብለዋል።

በኢጋድ የምግብ ሥርዓት ፕሮግራም አስተባባሪ ሰናይት ረጋሳ(ዶ/ር) በበኩላቸው የኢጋድ አባል ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የግብርና ስራ ለመስራት እያደረጉ ያለውን ጥረት የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል።

ፕሮግራሙ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የገበያ ትስስር በመፍጠር፣ የግብርና ፖሊሲዎች አሰሪ እንዲሆኑ እንዲሁም የተደራጀ የመረጃ ሥርዓት አያያዝ ላይ የቴክኒክ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

ግብርናን ማዘመንና በቴክኖሎጂ የማገዙ ስራ የበለጠ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

በቀጣናው የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች እያጋጠሙ መሆኑን ጠቅሰው በተለይም ግብርናው በአየር ንብረት ለውጥ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያርፍበት መሆኑን ጠቅሰዋል።

እንደ ዶክተር ሰናይት ገለጻ የቀጣናው ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ ያላቸው ድርሻ አነስተኛ ቢሆንም ዋነኛ የችግሩ ገፈት ቀማሽ ሆነዋል።

ይህንን ችግር ለመቋቋም ኢትዮጵያ የጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ለሌሎች ምሳሌ እንደሚሆን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የግብርና ኢንቨስትመንትን የበለጠ ለማሳደግ የጀመረቻቸው ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ በመድረኩ ተነስቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም