የህንድ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ እንዲሰማሩ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 13/2017(ኢዜአ)፦የህንድ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በጤና ዘርፍ እንዲሰማሩ አምባሳደር ፍሰሃ ሻውል ጥሪ አቀረቡ።

በህንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍስሀ ሻውል የተሳተፉበት የእስያ የቢዝነስ እና ሶሻል ፎረም ተካሄዷል።

ፎረሙ ከአፍሪካ፣ አሜሪካና እስያ የተወጣጡ ባለሀብቶች፣ ዲፕሎማቶች፣ የምርምር ተቋማት፣ ታዋቂ ግለሰቦች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በአንድ መድረክ ያገናኘ ሲሆን የዓለምን የቢዝነስ ስነ ምህዳር ላይ ለውጥ ማምጣት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።


 

በመድረኩ ላይ አምባሳደር ፍሰሃ ሻውል ኢትዮጵያ በዓለም ሶስተኛዋ የዲፕሎማሲ ማዕከል እና የአፍሪካ መግቢያ በር ናት ብለዋል።

መንግስት የተለያዩ ዘርፎችን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት በማድረግ የወሰዳቸውን እርምጃዎች አስመልክቶም ለፎረሙ ተሳታፊዎች ገለጻ አድርገዋል።

የኢኮኖሚ ኢኒሼቲቩ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በተለይም በጤና ክብካቤ እና የጤና ቱሪዝምን ለመሳብ ምቹ ሁኔታን የፈጠረ መሆኑን ገልጸው ይህም ኢትዮጵያ አፍሪካውያን ለጤና አገልግሎት የሚመርጧት ዋንኛ መዳረሻ እንድትሆን አድርጓታል ነው ያሉት።

የህንድ ባለሀብቶች ይህን ምቹ የኢንቨስትመንት እድል ተጠቅመው በኢትዮጵያ የጤና ክብካቤ እና የጤና ቱሪዝም መስኮች ላይ እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ፎረሙ ለዜጎች እና ተቋማት ዘላቂ ሀብት መፍጠር፣ የቴክኖሎጂ ለውጦች፣ የሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና የኢነርጂ ሽግግር ላይ ትኩረት በማድረግ መወያየቱን በኒው ዴልሂ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም