ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ህይወታቸውን ሙሉ ለጌታና ቤተክርስቲያን አገልግሎት የሰጡ ታላቅ እረኛ ነበሩ - ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል - ኢዜአ አማርኛ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ህይወታቸውን ሙሉ ለጌታና ቤተክርስቲያን አገልግሎት የሰጡ ታላቅ እረኛ ነበሩ - ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 13/2017 (ኢዜአ):- የሮማ ካቶሊክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ብፁዕ ወቅዱስ ፍራንሲስ ህይወታቸውን ሙሉ ለጌታና ቤተክርስቲያን አገልግሎት የሰጡ ታላቅ እረኛ ነበሩ ሲሉ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል ገለጹ።
የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በህክምና ሲረዱ ቆይተው በ88 ዓመታቸው በዛሬው ዕለት ከዚህ ዓለም ድካም ማረፋቸውን ቫቲካን አስታውቃለች፡፡
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ህልፈትን አስመልክቶ የሀዘን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም እግዚአብሔር የሚወዳቸውን እኝህን ታላቅ አባት በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ ማግስት ወደዘላለማዊ ማረፊያው ወስዷቸዋል ብለዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ባለፉት ወራት ባደረባቸው ከባድ ህመም ህክምና ሲከታተሉ እንደነበር በማውሳት፥ ትናንት በቫቲካን ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በመገኘት የትንሳኤን በዓል እና ለዓለም ሰላም የመልካም ምኞት መልዕክት ማስተላለፋቸውን ተናግረዋል።
ነገር ግን ዛሬ ጠዋት የቅድስት መንበር እረኛ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ከዚህ ዓለም ድካም ማረፋቸውን በመስማታችን ከባድ ሀዘን ተሰምቶናል ብለዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ህይወታቸውን በሙሉ ለጌታና ለቤተክርስቲያን አገልግሎት እረኛ እንደነበሩም ገልጸዋል።
የካቶሊክ ቤተክርስቲያንን በክህነት፣ በሊቀ-ጳጳስነት፣ በካርዲናልነት እንዲሁም በቅድስት መንበር እረኝነት በርካታ ሐዋሪያዊ አገልግሎቶችን ያበረከቱ አባት እንደነበሩም አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤም በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ህልፈት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከናወኑ የሀዘንና የሥርዓተ ቀብር መርሃ ግብሮች በቀጣይ ይፋ እንደሚደረጉም ተናግረዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ እ.አ.አ ታኅሣሥ 17 ቀን 1936 በአርጀንቲና ቦነስ አይረስ ከተማ ነበር የተወለዱት።