የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር በብፁዕ ወቅዱስ ፍራንሲስ ህልፈተ ህይወት የተሰማቸውን ሀዘን ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር በብፁዕ ወቅዱስ ፍራንሲስ ህልፈተ ህይወት የተሰማቸውን ሀዘን ገለጹ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 13/2017(ኢዜአ):- የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ በብፁዕ ወቅዱስ ፍራንሲስ ህልፈተ ህይወት የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል።
ሊቀ መንበሩ በሀዘን መግለጫ መልዕክታቸው ፖፕ ፍራንሲስ የዘመናችን ግዙፍ የሞራል መገለጫ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።
ለሰላም፣ ፍትህ፣ መልካምነት እና ለመንፈሳዊ መሪነት በጽኑ ሲተጉ የነበሩ መሪ ናቸው ብለዋል።
ፓፕ ፍራንሲስ ለሰላም በነበራቸው ጽኑ መሻት፣ ለተቸገሩ ወገኖች በሰጡት ትህትና የተሞላበት አገልግሎት፣ በአየር ንብረት ለውጥ በነበራቸው ጠንካራ ተሟጋችነት እንዲሁም የተለያየ ባህልና እምነት ባላቸው ማህበረሰቦች መካከል ምክክር እንዲኖራቸው በነበራቸው ትጋት ሁሌም ሲታወሱ እንደሚኖሩ አመልክተዋል።
በአፍሪካ ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ በመሆን፣ ሰላም እና እርቅ እንዲፈጠር እንዲሁም በግጭት እና ድህነት ከተጎዱ ሰዎች ጎን በመቆም ያሳዩትን አጋርነት አድንቀዋል።
ሊቀ መንበሩ ለሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን፣ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች እና በጎ ስራቸውን ለተከተሉ ሰዎች በሙሉ ልባዊ መጽናናትን ተመኝተዋል።