ባህር ዳር ከተማ ደረጃውን ወደ ሁለተኛ ከፍ ያደረገበት ወሳኝ ድል አስመዝግቧል 

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 13/2017(ኢዜአ):- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ26ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ባህር ዳር ከተማ መቀሌ 70 እንደርታን 4 ለ 1 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፏል። 

ማምሻውን በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ቸርነት ጉግሳ እና አቤል ማሙሽ በተመሳሳይ ሁለት ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል። 

አሸናፊ ሐፍቱ ለመቀሌ 70 እንደርታ ብቸኛዋን ጎል አስቆጥሯል። 

ድሉን ተከትሎ ባህር ዳር ከተማ በ40 ነጥብ ደረጃውን ከ3ኛ ወደ 2ኛ ከፍ አድርጓል። በውድድር ዓመቱም 11ኛ ድሉን ማስመዝገብ ችሏል። 

ከሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነትም ወደ ስምንት ዝቅ ማድረግ ችሏል።  

በሊጉ 10ኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው መቀሌ 70 እንደርታ በ28 ነጥብ 14ኛ ደረጃን ይዟል። 

ዛሬ በተደረጉ የ26ኛ ሳምንት ሌሎች ጨዋታዎች መቻል አዳማ ከተማን 2 ለ 0 እንዲሁም ድሬዳዋ ከተማ ፋሲል ከነማን 1 ለ 0 አሸንፈዋል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም