ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን በአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤው የአፍሪካ ድምጽ ጎልቶ እንዲሰማ በጋራ እንደሚሰሩ ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን በአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤው የአፍሪካ ድምጽ ጎልቶ እንዲሰማ በጋራ እንደሚሰሩ ገለጹ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 13/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን በሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ የአህጉሪቷ ድምጽ ጎልቶ እንዲሰማ ለማድረግ በጋራ እንደሚሰሩ አስታወቁ።
ሁለቱ ወገኖች በኢትዮጵያ የሚዘጋጀው ጉባኤ በስኬት ለማዘጋጀት እያከናወኑ የሚገኙትን ስራ የሚገመግም ስብሰባ አድርገዋል።
በውይይቱ ኢትዮጵያ እና ኮሚሽኑ ለጉባኤው እያደረጉት ያለው ስትራቴጂካዊ ዝግጅት ላይ ሀሳቦችን ተለዋውጠዋል።
ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ለአህጉሪቷ የአየር ንብረት ለውጥ ፈተናዎች ዘላቂ መፍትሄ የሚያበጅ ሆኖ ሁነት እንዲሆን አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ መንግስት እና የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን በጉባኤው ትርጉም ያለው ውጤት እና ለውጥ የሚፈጥር ውይይት እንዲካሄድ በጋራ እየሰሩ ይገኛሉ።
ጉባኤው የአፍሪካ ድምጽ ጎልቶ እንዲሰማ እና በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል የማይበገር አቅም መገንባት እና ዘላቂ ልማት የሚያረጋግጥ ስትራቴጂ መቅረጽ የሚያስችል መድረክ መፍጠር ላይ ትኩረት ማድረጉን የሚኒስቴሩ መረጃ ያሳያል።
ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በመስከረም ወር 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።