የንብ ማነብ ስራ የአብዛኛዎቹ አርሶ አደሮች ተግባር ነው

አንዳንዶቹ ከመደበኛ ግብርና ጎን ለጎን ያከናውኑታል ሌሎቹ ደግሞ ብቻውን የሙሉ ጊዜ ስራቸው መተዳደሪያቸው ያደርጉታል።

በደቡብ ምዕራብ ክልሏ ዳውሮ ዞን ሎማ ቦሳ ወረዳ በአንድ ቀበሌ ውስጥ ብቻ በ110 ዘመናዊ እና በ160 ባህላዊ የንብ ቀፎዎች እየተከናወነ ያለው የንብ ማነብ ስራ ውጤታማ እያደረጋቸው መሆኑን አርሶ አደሮቹ ይናገራሉ።

ኤላ ባቾ በተባለችው ቀበሌ ያሉት አርሶ አደሮቹ የማር ምርታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱም ተጠቃሚ አድርጓቸዋል።


 

የወረዳው ግብርና አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ ልማት ጽሕፈት ቤትም በዘርፉ ለተሰማሩ አርሶ አደሮች ሁለንተዊ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር እየሠራ መሆኑን ገልጿል።

በጽሕፈት ቤቱ እንስሳትና ዓሳ ዘርፍ ኃላፊ አቶ መስፍን ገበየሁ እንደሚያስረዱት ቀደም ሲል ከአንድ ባህላዊ ቀፎ ከ4 እስከ 5 ኪሎ ግራም ማር ይገኝ ነበር።

አሁን በስፋት እየተሰራበት ባለው የሽግግር ቀፎም ከ20 እስከ 25 ኪሎ ግራም ማር እየተገኘ መሆኑን ያስረዳሉ።

ለዚህ ደግሞ ከቀፎ አዘገጃጀት ጀምሮ እስከ ማር ቆረጣ ድረስ በዘርፉ ከተሰማሩ አርሶ አደሮች ጋር በመሆን ሙያዊ ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም