ዳያስፖራው በልማትና ኢንቨስትመንት በንቃት መሳተፍ እንዲችል ጠንካራ አደረጃጀት እየተዘረጋ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዳያስፖራው በልማትና ኢንቨስትመንት በንቃት መሳተፍ እንዲችል ጠንካራ አደረጃጀት እየተዘረጋ ነው

አዳማ፤ ሚያዝያ 16/2017(ኢዜአ)፦ዳያስፖራው በልማትና ኢንቨስትመንት በንቃት መሳተፍ እንዲችል ጠንካራ አደረጃጀት እየተዘረጋ መሆኑን የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍፁም አረጋ ገለፁ።
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበራት ህብረት ምስረታ ጉባኤ በአዳማ ተካሂዷል።
በምስረታ ጉባኤው የሁሉም ክልሎችና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የዲያስፖራ ማህበራትና የክልሎች የዳያስፖራ አስተባባሪዎች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍፁም አረጋ በተለይ ለኢዜአ አንደገለጹት፥ ዳያስፖራው በሀገር ውስጥና በውጭ ለሚኖረው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ ለማጎልበት ጠንካራ አደረጃጀት እንዲኖረው እየተሰራ ነው።
ጉባኤው በየክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች በተናጥል እየተንቀሳቀሱ ያሉ የዳያስፖራ ማህበራት በጋራ በህብረት የሚሰሩበትን ማህበር ለመመስረት ያለመ ነው ብለዋል።
በዚህም በየክልሎችና የውጪው ዓለም የሚገኙ የዳያስፖራ ማህበራት የጋራ ህብረት ፈጥረው ዕውቀት፤ ቴክኖሎጂ፤ ትምህርትና ሀብታቸውን ወደ ሀገር በማምጣት በኢንቨስትመንትና በልማቱ በመሳተፍ ራሳቸውና ሀገራቸውን እንዲጠቅሙ ለማስቻል መሆኑን አንስተዋል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት የዳያስፖራው ተሳትፎ መጨመሩን ጠቅሰው፥ በአበባ ልማት፤አትክልትና ፍራፍሬ፤ ቡናና ሌሎች ዘርፎች መሳተፍ እንደሚገባ ገልጸዋል።
በተጨማሪም በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ዳያስፖራው በንቃት እንዲሳተፍ እድል የተፈጠረ መሆኑን ጠቅሰው፥ አሁንም ዳያስፖራው በስፋት የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል ነው ብለዋል።
የኦሮሚያ ዳያስፖራ ማስተባበሪያ ዋና ዳይሬክተር አቶ አሚን ጁንዲ በበኩላቸው፥ በውጪ ዓለም ያሉ የክልሉ ተወላጆች በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት በንቃት እየተሳተፉ ይገኛሉ ብለዋል።
ባለፉት ሶስት ዓመታት ከ700 በላይ የዳያስፖራ አባላት በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች እየተሳተፉ ሲሆን በተለይ በትምህርት ቤቶች፤ ጤና ተቋማትና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ጭምር በመገንባት ለማህበረሰቡ አገልግሎት እንዲውል የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል።
የህብረቱ መመስረት በየክልሎቹ ያለውን የዳያስፖራ ማህበራት ጠንካራ አቅም በመፍጠር ከሀገር ባለፈ ዳያስፖራው ስለ ሀገሩ ወጥነት ያለው ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኝ የሚረዳ መሆኑን አንስተዋል።
የአዲስ አበባ ዲያስፖራ ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ዘለቀ ገሠሠ እንደገለፁት፥ ዳያስፖራው በሀገር ጉዳይ እየተሳተፈ መሆኑን አስታውሰዋል።
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ህብረት መደራጀት ወጥነት ያለውና ሁሉን አቀፍ የሆነ ጠንካራ አደረጃጀት ያለው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ እውን እንዲሆን የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪው ዓለም የተቀናጀና የተናበበ ስራ ለመስራት፤ ዳያስፖራው በኢንቨስትመንትና በሀገር ልማት ንቁ ተሳትፎ እንዲኖረው የሚያስችል መሆኑንም አመላክተዋል።
የህብረቱ መመስረት በሀገር ውስጥ ያሉትን ብቻ ሳይሆን በውጪ ያሉትን ዳያስፖራ በዕውቀት፤ በቴክኖሎጂ ሽግግር፤ በኢንቨስትመንትና በልማት እንዲሳተፉ ሰፊ የማነቃቃት ስራ ለመስራት ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም አስታውቀዋል።