የኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ ስኬት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተሞክሮ የሚሆን ነው- ሞሰስ ቪላካቲ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ ስኬት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተሞክሮ የሚሆን ነው- ሞሰስ ቪላካቲ

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 16/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ እያስመዘገበች ያለችው ስኬት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት እንደ መልካም ተሞክሮ የሚወሰድ መሆኑን የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ ብሉ ኢኮኖሚ እና ዘላቂ ከባቢ አየር ኮሚሽን ሞሰስ ቪላካቲ ገለጹ።
የግብርና ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ ብሉ ኢኮኖሚ እና ዘላቂ ከባቢ አየር ኮሚሽን ሞሰስ ቪላካቲ ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።
ሚኒስትሩም በውይይቱ ወቅት ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ተጨባጭ ለውጥ እያስመዘገበች እንደሆነ ገልጸዋል።
በስንዴ ልማት፣ በሌማት ትሩፋት እንዲሁም በአረንጓዴ አሻራ የተመዘገቡ ስኬቶችንም አንስተዋል።
ሚኒስትሩ አያይዘውም ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ የተመዘገቡትን ምርጥ ተሞክሮዎች ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ለማካፈል ቁርጠኛ ናት ብለዋል።
አፍሪካ በግብርናው ዘርፍ ያላትን የመልማት አቅም በመጠቀም የምግብ ዋስትና እና የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ይኖርብናል ብለዋል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ ብሉ ኢኮኖሚ እና ዘላቂ ከባቢ አየር ኮሚሽን ሞሰስ ቪላካቲ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ እያስመዘገበች ያለችው ውጤት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት እንደ መልካም ተሞክሮ የሚወሰድ ነው ብለዋል።
የአፍሪካን የምግብ ዋስትናና የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የልምድ ልውውጥን ጨምሮ በአፈር ማዳበሪያ፣ በምርጥ ዘር ብዜት፣ በግብርና ዲጂታላይዜሽን እንዲሁም በአፈር ካርታ (soil maping) ላይ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር መስራት እንደሚፈልጉ መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።