ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ የሆኑ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች የኢትዮጵያን እምቅ የቱሪዝም አቅም አደነቁ

አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 17/2017 (ኢዜአ)፦ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ የሆኑ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችና ከአለም አቀፍ ድርጅቶች የተወከሉ ልኡካን የኢትዮጵያን እምቅ የቱሪዝም አቅም አደነቁ።

ኢትዮጵያ የተለያየ ባህል፣ አመጋገብ፣ አልባሳት፣ የተፈጥሮ ጸጋዎችና ታይተው የማይጠገቡ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ቅርሶችን በስፋት የያዘች ሀገር ናት።

የቱሪዝም ሚኒስቴር ከዩኔስኮ ጋር በመተባበር ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ላደረጉ አምባሳደሮች የባሌ ተራሮች ብሄራዊ ፓርክን አስጎብኝተዋል።

የቱሪዝም ሀብቶቹን በስፋት ለማስተዋወቅና ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለማሳደግ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችና ከአለም አቀፍ ድርጅቶች የተወከሉ ልኡካን በዩኔስኮ የተመዘገበውን የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ጎብኝተዋል፡፡

አምባሳደሮችና ከአለም አቀፍ ድርጅቶች የተወከሉ ልኡካን በዚሁ ወቅት የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የኢትዮጵያን እምቅ የቱሪዝም አቅም ያዩበት መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የብሪታኒያ አምባሳደር ዳረን ዌልች ፓርኩ የስነ ህይወት ስብጥር እና አስደማሚ መልክዓ ምድሮችን የያዘ ቦታ መሆኑን መመልከታቸውን ተናግረዋል።

ፓርኩ እውነተኛ የተፈጥሮ ውበትን የተላበሰ የሰላም እና የመረጋጋት ስሜት የሚሰጥ ነው ያሉት አምባሳደሩ በሌላው የአለም ክፍል የማይገኙትን የተለያዩ የዱር እንስሳት መመልከታቸውን ገልጸዋል።

አምባሳደር ዳረን ዌልች ኢትዮጵያ ከፍተኛ የቱሪዝም አቅም ያላትና በዓለም ላይ ልዩ የሆነች ሀገር ናት ሲሉ አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ የሮማኒያ አምባሳደር ጁሊያ ፓታኪ በበኩላቸው የባሌ ተራራ ውበት አስደናቂ መሆኑንና ጉብኝታቸው አስደማሚ እንደነበር አንስተዋል፡፡

በጉብኝታቸው በኢትየጵያ ብቻ የሚገኘውን ኒያላን መመልከታቸውንም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሃብቶች ትኩረት የሚስቡ መሆናቸውን በመግለጽ በዩኔስኮ የተመዘገቡ የባህል ቅርሶችን እና የተለያዩ ስነ-ምህዳሮችን አወድሰዋል።

መንግስት የቱሪዝም ተደራሽነትን ለማሻሻል እያደረገ ያለውን አስተዋፅኦ አድንቀው የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ባህል እና ወጎች ለአለም ለማስተዋወቅ ቱሪዝም ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው በአጽንኦት አንስተዋል።

በኢትዮጵያ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ኖንሴባ ናንሲ ሎሲ ደቡብ አፍሪካ እና ኢትዮጵያ በተለይም በቱሪዝም ላይ ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

ሁለቱ ሀገራት በዩኔስኮ የተመዘገቡ የቱሪዝም ሃብቶችን በጋራ ማስተዋወቅ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ የዩኔስኮ ተወካይ ሪታ ቢሶኖውዝ ፓርኩ የተላበሰው አረንጓዴ ውበትና በውስጡ የያዛቸው የዱር እንስሳት ከሚጠበቀው በላይ አስደናቂ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ጉብኝታቸው ይህን ውብ ቦታ ለአለም ለማስተዋወቅ ያለመ መሆኑን አንስተው እነዚህ ቦታዎች በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ በስፋት እንዲተዋወቁ ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ መንግስት በልዩ ትኩረት እየሰራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የ"ለሀገር እራት እንብላ" ፕሮጀክትን ጨምሮ በርካታ ስኬታማ ስራዎች መሰራታቸውን አንስተው፥ በቱሪዝም መሠረተ ልማት ላይ የግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት እያደገ መሆኑንም አንስተዋል።

በኢትዮጵያ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ 17 ቦታዎች እና ከ10 በላይ ብሔራዊ ፓርኮች እንዳሉ ጠቅሰው፥ እነዚህን ሃብቶች ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስተዋወቅ አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም