ሁለተኛው ዙር የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ከሰኔ ወር ጀምሮ ይካሄዳል - ኢንጅነር ለሊሴ ነሜ

አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 17/2017 (ኢዜአ)፡-ሁለተኛው ዙር የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ጽዳትና የአካባቢ ጥበቃ ስራን ባህል ማድረግ በሚያስችል መልኩ ከመጪው ሰኔ ወር ጀምሮ ለስድስት ወራት እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ለሊሴ ነሜ አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሚያዚያ 18/2016 ዓ.ም ጽዱ ኢትዮጵያን ለመፍጠር ያለመ "የጽዱ ኢትዮጵያ" ንቅናቄን በይፋ ማስጀመራቸው ይታወሳል።

በንቅናቄው በርካታ ኢትዮጵያውያን የተሳተፉበት የከተማ ጽዳትና ውበት የገቢ ማሰባሰቢያ ጨምሮ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ተካሂደዋል።

የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ለሊሴ ነሜ÷ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተተገበሩ የአረንጓዴ አሻራና የኮሪደር ልማት መርሃ ግብሮች ለአካባቢ ጥበቃና ጽዱ ኢትዮጵያ ገንቢ ሚና እየተወጡ ነው ብለዋል።

የመጀመሪያው ዙር የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄም የፕላስቲክ፣የአየር፣ የውሃ፣የአፈርና የድምጽ ብክለትን መከላከል እንዲሁም የአካባቢና ማህበራዊ ተጽዕኖ ሰነዶች ግምገማ መድረክ መካሄዱን አስታውሰዋል።

በዚህም ዜጎች ጽዳትና የአካባቢ ጥበቃ ስራን ባህል እንዲያደርጉ ግንዛቤ የተፈጠረበት ነው ብለዋል።

በተጨማሪም በጽዳትና በአካባቢ ጥበቃ አሰራር ሥርዓት ላይ የሚስተዋሉ የሕግ ክፍተቶችን በመፈተሽ የማሻሻልና ተፈፃሚ የማድረግ አቅምን ማጎልበቱን ተናግረዋል።

በመጀመሪያው ዙር ጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ የመንግስት፣ የኃይማኖትና የግል ተቋማትን ጨምሮ ከ7 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ዜጎች ተሳትፎ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ብክለትን የመከላከልና የአካባቢን ንጽህና የመጠበቅ ጉዳይ ቁልፍ አጀንዳ መሆኑን መግባባት በመፍጠር ወደ ትግበራ የተገባበት ነው ብለዋል።

ሁለተኛው ዙር የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ መርሃ ግብርን "ከዓለም አቀፍ የአካባቢ ቀን" ጋር በማስተሳሰር ከመጪው ሰኔ ወር ጀምሮ ለስድስት ተከታታይ ወራት እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።

በዚህም በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በግንዛቤ ፈጠራ፣ በሕግ ተከባሪነትና ለአካባቢ ደህንነት ጥሩ የሰሩ የሚመሰገኑበት መርሐግብር ይካሄዳል ብለዋል።

መርሃ ግብሩን ስኬታማ ለማድረግ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን (ኢዜአ) ጨምሮ ከሌሎች መገናኛ ብዙኃንና ኢንዱስትሪዎች ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ንቅናቄው የኤሌክትሮኒክስ፣የአደገኛ ኬሚካልና ደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ፣ የውሃና የአፈር፣ የአየርና የድምጽ ብክለት መከላከል ሥራ የሚከወንበት እንዲሁም የአካባቢና ማህበራዊ ተጽዕኖ ግምገማ የሚደረግበት መሆኑን አስረድተዋል።

በገፅ ለገፅ መርሐ ግብሮች 15 ሚሊዮን ዜጎችን በማሳተፍ ጽዳትና የአካባቢ ጥበቃን ባህል ያደረገ ትውልድ ለመገንባት እንደሚሠራም ተናግረዋል።

የችግኝ ተከላ እና መንከባከብ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሥራዎች እንደሚከናወኑም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም