ጽምዶ የተባለው ሀይል በሰሜን ኢትዮጵያ የደረሰበትን ከባድ ሽንፈት ለመሸፈንና ትኩረት ለማስቀየር የብሔር እና የሃይማኖት ግጭት ለመፍጠር ያደረገው እንቅስቃሴ ከሽፏል - አቶ ሃይሉ አዱኛ - ኢዜአ አማርኛ
ጽምዶ የተባለው ሀይል በሰሜን ኢትዮጵያ የደረሰበትን ከባድ ሽንፈት ለመሸፈንና ትኩረት ለማስቀየር የብሔር እና የሃይማኖት ግጭት ለመፍጠር ያደረገው እንቅስቃሴ ከሽፏል - አቶ ሃይሉ አዱኛ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 15/2019 (ኢዜአ)፦ ጽምዶ የተባለው ሀይል በሰሜን ኢትዮጵያ የደረሰበትን ከባድ ሽንፈት ለመሸፈንና የትኩረት አቅጣጫ ለማስቀየር የብሔር እና የሃይማኖት ግጭት ለመፍጠር ያደረገው እንቅስቃሴ መክሸፉን የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ ሀይሉ አዱኛ ገለጹ።
አቶ ሀይሉ አዱኛ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ሀገራችን እያመጣች ያለውን እድገት በማስተጓጎል ሰላም እና ጸጥታን ለማናጋት የጠላት ኃይሎች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ፈጽሞ የማይሳካ መሆኑን ገልጸዋል።
አቶ ሃይሉ፤ እነዚህ የጥፋት ሀይሎች እየደረሰባቸው ባለው ከፍተኛ ሽንፈት የመንግሥትን የትኩረት አቅጣጫ ለማስቀየር እና የውስጥ ግጭቶችን ለማስፋፋት እየተፍጨረጨሩ መሆኑን ተናግረዋል።
የሸፍጥ እና የውድመት ሥራ ላይ የተሰማራው የጽንፈኛ ቡድን በደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ ዞን በሰሸርካ ወረዳ በቾሌ እና ብርቦ ቀበሌዎች በንጹሐን ሕይወት እና ንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል ብለዋል።
በዚህም የኦሮሚያ ክልል መንግሥት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን እየገለጸ፤ እነዚህን አጥፊ አካላት ላይ ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን የጀመረውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ሃይሉ ገልጸዋል።
የክልሉ መንግሥት በዚህ ችግር ምክንያት ለተጎዱ እና ከቀዬአቸውና ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች ከሕብረተሰቡ ጋር በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።