ቀጥታ፡

የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክት በራስ የመልማት አቅማችንን ያሳየንበት ነው-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 15/2019 (ኢዜአ)፦ዛሬ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት የተደረገው የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክት እንችላለን የሚለውን እምነት በተግባር ያረጋገጥንበት እና በራስ የመልማት አቅማችንን ያሳየንበት ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ።

የቀጨኔ፣ አምባሳደር፣ ጊዮን-ኢሬቻ እና ባምቢስ የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።


 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ፕሮጀክቱ ቀደም ሲል በብክለት እና በትኩረት ማጣት ተጎድተው የነበሩ የወንዝ ዳርቻዎችን መልሶ በማልማት ለከተማዋ ነዋሪዎች ጤናማ፣ ምቹ እና ማህበራዊ አገልግሎት የሚሰጥ አካባቢን የመፍጠር ዓላማ ያነገበ ነው።

ከንቲባዋ አክለውም፣ ፕሮጀክቱ እንችላለን የሚለውን እምነት በተግባር ያረጋገጥንበት እና በራስ የመልማት አቅማችንን ያሳየንበት ነው ብለዋል።

በኮሪደሩ መስመር 16 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ደረጃውን የጠበቀ የአስፋልት መንገድ መገንባቱንም ገልጸዋል።

አካታች ልማት እንደመሆኑ መጠን የእግር ጉዞ የሚያበረታቱ 22 ኪሎ ሜትር የእግረኛ መንገድ፣ 20 ኪሎ ሜትር የሳይክል መንገድ እና 5 ኪሎ ሜትር የመሮጫ ትራክ መሠራቱንም ተናግረዋል።

በተጨማሪም ከአንድ ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ የሚችሉ 22 የፓርኪንግ ስፍራዎች እና ከመቶ በላይ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በጋራ ማስተናገድ የሚችሉ 8 የቻርጅ ጣቢያዎች መገንባታቸውን ከንቲባዋ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል 18 የተሽከርካሪ ድልድዮች (5 ነባር እና 13 አዳዲስ) እንዲሁም 23 የእግረኛ እና የሳይክል መሸጋገሪያ ድልድዮች በድምሩ 41 ድልድዮች መገንባታቸውን ገልጸዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የከተማዋን ጎርፍ እና ብክለት ለመከላከል የሚያስችሉ የፍሳሽ እና የጎርፍ መውረጃ መስመሮች ተገንብተው በዛሬው ዕለት ለአገልግሎት ክፍት መሆናቸውን አስታውቀዋል።

በአካባቢ ጥበቃ ረገድም በ351 ሄክታር መሬት ላይ የአፈር ጥበቃ እና የእርከን ሥራዎች የተከናወኑ ሲሆን፣ ከ300 ሺህ በላይ ሀገር በቀል ችግኞች መተከላቸውን ገልጸዋል።


 

የሕዝብ መዝናኛዎችን ለማስፋፋትም 8 የውሃ ትርኢቶች (ፋውንቴኖች)፣ ፓርኮች እና መዝናኛዎች መዘጋጀታቸውን ከንቲባዋ ተናግረዋል።

በዚህም በቋሚነት እና በጊዜያዊነት ከ56 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል ብለዋል ። 

በንግድ መስመሩ ላይ 30 ካፌዎች እና 185 ሱቆች መገንባታቸውን አንስተዋል።

በተጨማሪም በቀጨኔ አካባቢ የእጅ ጥበብ እና የባህል ሥራዎች መሸጫ የሚሆን 108 ሱቆችን፣ ባንክ እና ካፌዎችን ያካተተ ትልቅ የገበያ ማዕከል ተገንብቶ ለአገልግሎት በቅቷል ብለዋል።

ህብረተሰቡ የተገነቡትን የመሠረተ ልማት አውታሮች በባለቤትነት ስሜት፣ በሰለጠነ እና በተገቢው አግባብ በጥንቃቄ ሊገለገልባቸው እንደሚገባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም