የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የዛሬ ተጠባቂ ጨዋታዎች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የዛሬ ተጠባቂ ጨዋታዎች
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 16/2019 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አራተኛ ሳምንት የሶስተኛ ቀን ውሎ አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ጋሞ ጨንቻ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ አባያ ካምፓስ ስታዲየም ይጫወታሉ።
አዲስ አዳጊው ጋሞ ጨንቻ በሊጉ ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግዶ ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻውን 18ኛ ደረጃን ይዟል።
ከሶስት ጨዋታዎች ሰባት ነጥብ ያገኘው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሊጉን እየመራ ነው።
ሁለቱ ክለቦች በሊጉ ሲገናኙ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
አንድ ተስተካካይ መርሐ ግብር ያለው ጋሞ ጨንቻ የመጀመሪያ ሶስት ነጥቡን ለማግኘት ይፋለማል።
በሶስተኛ ሳምንት ከሀዋሳ ከተማ ጋር አንድ አቻ የተለያየው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ ድል ከቀናው የሊጉን መሪነት ያጠናክራል።
በሌላኛው መርሐ ግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሸገር ከተማ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
የ16 ጊዜ የሊጉ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሶስት ጨዋታዎች ሁለት ነጥብ በማግኘት 13ኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ሸገር ከተማ በበኩሉ በአራት ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ሶስት ነጥቡን ለማግኘት ይጫወታል።
በሶስተኛ ሳምንት በኢትዮ ኤሌክትሪክ የ1 ለ 0 ሽንፈት ያስተናገደው ሸገር ከተማ ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ይፋለማል።
ሌላኛው መርሐ ግብር ነገሌ አርሲ እና አዳማ ከተማን ከቀኑ 9 ሰዓት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ያገናኛል።
ነገሌ አርሲ በአምስት ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። አዳማ ከተማ በተመሳሳይ አምስት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጦ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በሶስተኛ ሳምንት መርሐ ግብር ኢትዮጵያ ቡናን 3 ለ 0 በማሸነፍ የመጀመሪያ ድሉን ያሳካው ነገሌ አርሲ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታል።
አዳማ ከተማ በሶስተኛ ሳምንት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አንድ አቻ የተለያየ ሲሆን ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይፋለማል።
ምሽት 12 ሰዓት ላይ ወላይታ ድቻ ከሀላባ ከተማ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
ወላይታ ድቻ በሁለት ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
አዲስ አዳጊው ሀላባ ከተማ በአምስት ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል።
በሶስተኛ ሳምንት ወላይታ ድቻ በባህር ዳር ከተማ የ3 ለ 1 ሽንፈት ሲያስተናግድ ሀላባ ከተማ ከፋሲል ከነማ አንድ አቻ ተለያይቷል።
ጨዋታው ወላይታ ድቻ የመጀመሪያ ሶስት ነጥቡን ለማግኘት፣ ሀላባ ከተማ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ነው።