ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በመደመር እሳቤ የሴቶችና ወጣቶችን የፖለቲካ ውሳኔ ሰጪነት በማጠናከር ለአፍሪካ ዘላቂ ሰላምና ብልፅግና ሚናዋን እየተወጣች ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 26/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በመደመር እሳቤ የሴቶችና ወጣቶችን የፖለቲካ ውሳኔ ሰጪነት በማጠናከር ለአፍሪካ ዘላቂ ሰላምና ብልፅግና ሚናዋን እየተወጣች መሆኑን የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር አክሊሉ ታደሰ (ዶ/ር) ገለጹ።

ሁለተኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

ጉባዔው ከዛሬ ጥቅምት 26 ቀን 2019 ዓ.ም ጀምሮ "ዕድገትን መምራት ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ የአፍሪካ መጻኢ ኢኮኖሚ መሀንዲሶች" በሚል መሪ ሃሳብ ለሶስት ቀናት በዓድዋ ድል መታሰቢያ ይካሄዳል።

በዛሬው ዕለትም የአፍሪካ ሴቶችና ወጣቶች የፖለቲካ አመራር የጋራ ፎረም መክፈቻ መርሃግብር እየተካሄደ ይገኛል።


 

የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር አክሊሉ ታደሰ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት፤ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ለመጡ የፎረሙ ተሳታፊ ሴቶችና ወጣቶች ወደ ምድረ ቀደምቷ ኢትዮጵያ እንኳን በደህና መጣችሁ ብለዋል።

የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ "ዕድገትን መምራት ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ የአፍሪካ መጻኢ ኢኮኖሚ መሃንዲሶች" የሚለው መሪ ሀሳብ የአፍሪካ ወቅታዊና የትኩረት አጀንዳ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ጉባኤው አፍሪካውያን ለጋራ ዓላማቸው የሚያግዙ ተቋማትን ለማጠናከር፣ የበለጸገች አፍሪካን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስረከብ ቁልፍ ሚና አለው ብለዋል።

የአፍሪካ መፃኢ ዕድል በሴቶችና ወጣቶች ንቁ ተሳትፎ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ገልጸው፤ የአፍሪካ ወጣቶች የአሕጉሪቱ የሽግግር ሞተሮች፣ የሰላምና የጥንካሬዋ ምንጮች ናቸው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የአመራር ቦታዎች ላይ የሴቶችና የወጣቶች ተሳትፎ ከፍተኛ ነው ብለዋል።


 

በተጨማሪም በኢኖቬሽን፣ በኢንተርፕረነርሽፕ፣ በሥራ ፈጠራ እና በአመራር ቁልፍ ሚና እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ያለ ወጣቶች ተሳትፎ ብሔራዊ ብልፅግና ማምጣት አይቻልም የሚል አቋም እንዳላት ገልጸው፤ ወጣቶች የለውጥ መሀንዲሶች ናቸው ብለዋል።

ወጣቶችና ሴቶችን ከማሳተፍ ባለፈ እምነት በመጣል አካታችነትና ውሳኔ ሰጭነታቸውን ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

በቴክኖሎጂ ሽግግርና የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ለማረጋገጥ ሴቶችና ወጣቶች በአስተዳደርና አመራር በበቂ መሳተፍ አለባቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ በመደመር መንግሥት እሳቤ በአንድነት ስኬትን ማምጣት ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ለሰላማዊና የበለፀገች አፍሪካ ወጣቶች ቁልፍ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም