ቀጥታ፡

የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት እና ባለሙያዎች ለብሔራዊ ጥቅም ቅድሚያ ሰጥተው ሊሠሩ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 26/2019 (ኢዜአ)፦ መገናኛ ብዙኃን እና ባለሙያዎች በሥራዎቻቸው ለብሔራዊ ጥቅም ቅድሚያ ሰጥተው ሊሠሩ እንደሚገባ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል እና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የቦርድ ሰብሳቢ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለጹ።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ያስገነባው የኢትዮጵያ ሚዲያ የልኅቀት ማዕከል የምርቃት ሥነ ሥርዓት እየተካሄደ ነው።

በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል እና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የቦርድ ሰብሳቢ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን አመራር አባላትን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ማዕከሉ የጋዜጠኝነትና የመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ አቅምን ለማጎልበት ያለመ ሲሆን፣ የጋዜጠኞችን እና የመገናኛ ብዙኃን አመራሮችን እውቀት፣ ክህሎትና የሥነ ምግባር ደረጃ ማሻሻል ከተቋቋመባቸው ዓላማዎች መካከል ይገኝበታል።

የሚዲያ ዘርፉን በጥናት መደገፍ እንዲሁም የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን የሚያሳድጉ ሥልጠናዎችን ተደራሽ ማድረግም የማዕከሉ ሌላው ዓላማ ነው።

ኅብረተሰቡ የሐሰተኛ መረጃዎችን እና የጥላቻ ንግግርን መለየት የሚችልበትን ግንዛቤ መፍጠር ማዕከሉ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል ይገኝበታል።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል እና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የቦርድ ሰብሳቢ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የመናገር ነፃነት ከተጠያቂነት ጋር አብሮ የሚሄድ ነው።

መንግሥት ምህዳሩን ምቹ ለማድረግ ብዙ ሠርቷል ያሉት አምባሳደሩ፤ በዚህ ሂደት ሕጉን ተከትለው የሚሠሩ እንዳሉ ሁሉ፣ ጥቂት የሚባሉት መርሕን ጠብቀው የማይሠሩ መኖራቸው መለየቱን አንስተዋል።

ከተቀመጠው አሠራር ውጭ የሚሠሩት ላይ ክትትል በማድረግ ወደ ሕጋዊ መስመር እንዲገቡ እየተደረገ ነው ብለዋል።

የሚዲያ ባለሙያዎችም ሆኑ ተቋማት ሥራዎችን ከማሰራጨታቸው በፊት ትክክለኛ መርሆዎችን የተከተሉ መሆናቸውን ከኢትዮጵያ ፍላጎትና ከሕዝብ ጥቅም አኳያ መመዘን እንደሚገባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።

በሀገር ግንባታ ሂደት የመገናኛ ብዙኃን ገንቢ ሚና ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህም ተቋማትና ባለሙያዎች ትልቅ ሚና እንዳላቸው አስገንዝበዋል።

የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትን አቅም ለመገንባት ውጤታማ ሥራዎች መጀመራቸውን ጠቁመው፣ የኢትዮጵያ ሚዲያ የልኅቀት ማዕከል ከሥራዎቹ መካከል አንዱ መሆኑን አስረድተዋል።

ዛሬ ያስመረቀነው የሚዲያ ልኅቀት ማዕከል የክህሎት ክፍተትን በመሙላት ረገድ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ሲሉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃይማኖት ዘለቀ በበኩላቸው፤ ማዕከሉ ሥልጠናዎችን መስጠት የሚያስችል ዝግጅት ማጠናቀቁን አመልክተው፣ በቅርቡ ሥልጠና መስጠት ይጀምራል ብለዋል።

ለዚህም አስፈላጊው የሥልጠና ሞጁሎች ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸው፤ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የታገዙ ሥልጠናዎችም ተደራሽ ይደረጋሉ ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም፣ ዲፕሎማሲ እና የዘርፍ ጋዜጠኝነት ሥልጠናዎች በሥልጠና መርሃ ግብሩ ከተካተቱ ጉዳዮች መካከል እንደሚገኙ ተናግረዋል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም