ጉባኤው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለአህጉሪቱ ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ እድገት የላቀ ሚና እንዲወጡ የሚያስችል ነው - ኢዜአ አማርኛ
ጉባኤው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለአህጉሪቱ ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ እድገት የላቀ ሚና እንዲወጡ የሚያስችል ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 26/2019 (ኢዜአ)፦ ሁለተኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ የአህጉሪቷ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለአህጉሪቱ ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ እድገት የላቀ ሚና እንዲወጡ የሚያስችል መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለጹ።
2ኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ "ዕድገትን መምራት፤ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ የአፍሪካ መጻኢ ኢኮኖሚ መሐንዲሶች" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል መታሰቢያ መካሄድ ጀምሯል።
ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ቀናት የሚቆየው ጉባኤ አካል የሆነው የአፍሪካ ሴቶችና ወጣቶች የፖለቲካ አመራር የጋራ ፎረም 2026 የመክፈቻ መርሃ ግብር ተደርጓል።
የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ እየተካሄደ የሚገኘው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ ፓርቲዎች ለአህጉሪቱ ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ እድገት፣ ለልማትና ለዜጎች ኑሮ መሻሻል የላቀ ሚና እንዲወጡ የሚያስችል መሆን ተናግረዋል።
ጉባዔው ገዥም ሆኑ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሀገራቸው የኢኮኖሚ ሽግግር (ትራንስፎርሜሽን) እና የልማት ዕድሎች ያላቸውን ሚና አውቀው በትብብር እንዲሰሩ ለማስቻል ያለመ መድረክ ነው ብለዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ወቅት ድምፅ ለማግኘትና መንግሥት ለመመስረት ከሚያደርጉት ፉክክር ባሻገር፣ ድህነትን በመቀነስ፣ የስራ ዕድል በመፍጠርና የዜጎችን ህይወት በመለወጥ ረገድ የጋራ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው በመድረኩ መመላከቱን ጠቅሰዋል።
በዋናው መድረክ ዋዜማ የተጀመረው የወጣቶችና የሴቶች መድረክም ሴቶች እና ወጣቶች በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲሁም በአመራር ሰጪነት ያላቸውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማሳደግ በሚቻልባቸው ቁልፍ ጉዳዮች ላይ እየመከረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ይህ ውይይት የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመደራጀት ባለፈ ለአህጉሪቱ ዘላቂ ልማትና የህዝቦች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ ትልቅ ፋይዳ ያለው ሲሆን፣ የውይይቱ ማጠናቀቂያም የጋራ የአቋም መግለጫ (ዲክላሬሽን) በማውጣት እንደሚጠቃለል ገልጸዋል።